ረቡዕ 6 ጃንዋሪ 2016

“ ሕፃን ተወልዶልናልና”



በስመ አብ ወወለወድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
“ ሕፃን ተወልዶልናልና”
ልደታት ብዙ አሉ ፡፡ ልደተ አዳም ከምድር ልደተ ሔዋን ከአዳም ፣ልደተ ሙታን ከመቃብር ልደተ ሕፃናት ከእናታቸው ማህፀን የሚጠቀሱት ናቸው፡፡የእነዚህ ሁሉ ልደት ለራሳቸው ኢነጂ ለእኛ አይደሉም “ህፃን ተወለልዶልናል የሚለው ግን ለእኛ ነው፡፡”የአምላክን መወለድ ብዙ ነቢያት በብዙ ሕብረ ትንቢት ተናግረዋል በብዙ ሕብረ አምሳል መስለዋል፡፡”ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ አይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን  በነቢያት ተናግሮ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ዳግምም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን “ ዕብ1፣1 በብዙ ሕበረ አምሳል በብዙ ሕብረ ትንቢትእግዚአብሔር ከተናገረባቸው ነቢያት አንዱ ኢሳይያስ ነው ኢሳይያስ ከነቢያት ወንድሞች በተለየ መልኩ የአምላክን ሰው መሆን የተናገረ ነቢይ ነው ፡፡መወለዱን፣ስሙን፣ከማን እነደሚወለድ ፣ለሰው ልጆች ያደረገውን የቤዛነት ስራ መከራ መቀበሉን ፣በጎል መወለዱን በግልፅ ከተናገሩ የተነሳ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያ ወንጌላዊ ነቢይ የሚል ቀጽል ሰጥተው ይጠሩታል፡፡የትንቢት መጽሐፉንም ደረቅ ሐዲስ በማለት ሰይመውታል፡፡ይህም ማለት ስለክርስቶስ መወለድ በምሰሌ ያይደለ በቀጥታ የተናገረ በመሆኑ ነው  ለምሳሌ የሚከተሉትን ማየት ይቻላል፡፡
“ጌታ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅንም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች”ኢሳ 7፣14 ከላይ ባጭሩ እንዳየነው ከማን እንደምትወልድ ስሙን ማን አንደሆነ በግልጽ እስቀምጸጧል ፡፡ኢሳይያስ ቃል በሉቃ 1፣26 የምናየው ነው ፡፡በስድስተኛው ወር ገብርኤል መላክ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ ከዳዊት ወገን የሆነ ስሙ ዮሴፍ ለሚባል ሰው  ከታጨች ከድንግል  ዘንድ የዚህች ድንግል ስሟ ማርያም  ነው” በማለት  ወንጌለዊው ገልጧል “በነቢይ ከጌታ ዘንድ እነሆ ድንገል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለውን ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኗል ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው ማቴ 1፣22 ኢሳይያስ “ሕፃን ተወልዶልናል”ብሎ ለእኛ መዳን የተወለደው ነገረን ቀጥሎም ወንድ ልጅ ተሰጥቶናል “ ይላል ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን መድኃኒት ለሆነን እንደመጣ ሊያሳይ ፡፡ ከዚህ በመቀጠል እርሱን ለመግለጥ የተጠቀማቸው ቃላት በጣም የሚደንቁ ናቸው፡፡


1.      ስሙ
2.      ድንቅ
3.      መካር
4.      ኃያል
5.      አምላክ
6.      የዘላዓለም አባት
7.      የሰላም አለቃ
በሚሉ ሰባት ቃላት ገልጾታል ቁጥሩ በእብራዊያን ዘንድ ፍጹም ነው ከላይ ኢሳይያስ የተጠቀማቸው ሰባት ቃላት ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን የሚያስረዱ ናቸው ፡፡ሕፃን ብሎት ነበር ሕፃን የሚለው ስም ታህታዊ ማንም በሥጋ የወለደ ሰው ሲወለድ የሚጠራበር ነው ፡፡ ሰው መሆኑን ለመግለጥ ሕጻን አለው አምላክነቱን ለማስረዳት ስሙም ብሎ ጀምሮ በሰባት ቃለት አስረድቶናል፡፡
1.      ስሙ
ስለ ስሙ ቅዱሳት መጻፍት ሲናገሩ ኢየሱስ ፣አማኑኤል፣ ክርስቶስ ፣መድኃኔዓለም የሚባሉት ስመ ስጋዌ ናቸው ሰው በመሆኑ የተጠራባቸው ኢየሱስ ማለት መድሐኒት ማለት ነው፡፡ አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው ከእኛ ጋር ሲባል ከስጋችን ሥጋ ከደማችን ደምን ነስቶ ሰው የሆነ አምላክ ማለት ነው ክርስቶስ ማለት መሲህ ፣ሹም፣ንጉሥ ፣አለቃ ማለት ነው፡፡ መድኃኔዓለም ማለት የአለም መድኃኒት  የዓለም ቤዛ ደሙን አፍስሶ ሥጋውን ቆርሶ በደሙ ዓለምን የዋጀ ማለት ነው፡፡
“ልጅም ትወልዳለች እርሱም ሕዝቡን ከኃጢያታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለች” ማቴ 1፣21
“ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ እርሱ በመጣ ጊዜ ሁለን ይነግረናል አለችዉ ኢየሱስም የምትናገሪዉ እርሱ እኔ ነኝ አላት”ዮሐ 1፣42
“እኛ ራሳችን ሰምተነዋል አርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት  እንደሆነ እናውቃለን “ዮሐ 4፣42
ከላይ የተመለከትናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስሙንና ግብሩን የሚገልጡ ናቸው፡፡ትርጉሙ ከተግባር ጋር የተያያዘ ነውና ይህንን ነው ኢሳይያሰ “ሕፃን ተወለደልን” በማለት የተነገረለት ኢሳይያስም ሕጻን ብሎ የጠራዉ ሰዉ ሲሆን አምላክነቱ አልተለወጠምና አምላክነቱን መግለጥ የሚችሉ ቃላት ከስሙ ጀምሮ ተጠቅሟል
ስሙ አዳኝ ነው፡- አቤቱ በስምህ አድነኝ መዝ 53፣1
ስሙ ቅዱስ ነው፡- እርሱ ለእኔ ታላቅ ስራ አድርጎል እና ስሙም ቅዱስ ነው ሉቃ 1፣50
ስሙ ፡- አጋንንትን ይገዛል “አጋንንት በስምህ ተገዙልን” ሉቃ 10፣17
ያመኑትን  እነዚህን ምልክቶች ይከተሏቸዋል በስሜ አጋንትን  ያወጣሉ እባቦችን ይይዛሉ የሚያሰክር መርዝ ቢጠጡ አይገድላቸውም ማር 16፣17
ስሙ፡- ስግደት የሚገባው ነው “እግዚአብሔር/እግዚአብሔርነቱ/ ያለልክ ከፍ ከፍ አድርገው ከስምም ሁሉ በላይ ያለዉን ስምሰጠው ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይንበርከኩ ዘንድ”ቆላ 2፣9-11
ስሙ ምስጋና ይገባዋል”በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ”ማቴ 6፣9
2.      ድንቅ
ድንቅ ማለት ቃል እነደሚገባው አድርጎ የማይገልጠዉ ቃላት ላጣንለት ነገር የምንጠቀመዉ ነዉ በህቱም ድንግልና ተጸንሶ በህቱም ድንግልና መወለዱን ሲደንቅ የሚኖር ነውና በኪሩቤል ላይ የሚገለጥ ስጋን ለብሶ መወለዱን የማይወስነዉ መወሰኑ የማይዳሰሰው መዳሰሱ የማይታየው መታየቱ  የማይጨበጠው እሳተመለኮት በጨርቅ መጠቅለሉ በጎል መጣሉ የሚደንቅን ነው እነኳን ለኢሳይያስ ለመላእክትም ድነቅ ነው ሰማይ ዙፋኑ የሆነ አምላክ በትህትና መገለጡ ድሆች እንኳ ባልተወለዱበት የከብቶቸች በረት መወለዱ ድንቅ ነው፡፡
“በልዎ ለእግዚአብሔር ግሩም ግብርከ”እግዚአብሔርን ስራህ ድንቅ ነው በሉት መዝ65፣3 ሕፃናትን በእናታቸው ማህጸን የሚጠብቃቸው ሕጻን ሆነ ይህ እንዴት አይደንቅ
 “ስራህ ድንቅ ነው ነፍሴም እጅግ ታዉቀዋለች” መዝ 138፣12 በላይ በሰማይ በኪቤል ጀርባ በምድር በእናቱ እቅፍ መታየቱ ድንቅ ነው?
“ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ ለዓይናችን ድንቅ ነው” መዝ 117፣22 ማቴ 22፣42
3.      መካር
ሰው ለመሆን መወሰኑን በልብ የመከረውን በነብያት ያናገረውን ያን የፈጸመ ምክረ ከይሲን በምክሩ የሻረ ዲያብሎስን ያሣፈረ በልቡ ጥበብ ከሰው ልጆች በተለየች ምክሩ አዳምን ነጻ ያወጣ መካር ነው፡፡”ግሩም ምክሩ እምጎለመኸያው”ምክሩ ከሰው ልጆች ይልቅ ልዩ ነው  “መዝ 65፣5 በዚህ በልዩ ምክሩዲያብሎስ የመከራቸውን የነፍስና የስጋ ተዋህዶ በሥጋ ተወለደ ይህ የዲያብሎስን ስራ ያፈርስ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ ተገለጠ 1ተሰ3፣7
“ውዕቱ ጥበቡ ወምክሩ ያድኅነነ መጸአ “          እርሱ የአብ ጥበቡና ምክሩ ሊያድነን መጣ” ይለዋል ቅዱስ ያሬድ
4.      ኃያል
ኃያልነት የበሕርይ ገንዘቡ ነው “ኀይሉ ለአብ ወጸጋ ለአህዛብ…”የአብ ኃሉ እርሱ ነው ለአህዛብም ጸጋን የሚሰጥ “ እነዳለ መጽሐፈ ኪዳን ፡፡ መንግሥትህ ያንተ ናትና ኃይል ምስጋና ክብር ለዘላለሙ” ማቴ 6፣13 በኃይሉ ኃይለኛው ቤት ገብቶ ዕቃዉን ሊነጥቀዉ እንዴት ይቻላል ማቴ12፣29
“ክርስቶስም ስለ አናንተ አይደክምም /ደካማ /አይደለም ነገር ግ ን በእናንተ ኃለኛ ነው በድካም ተስቅሏልና ነገር ግን በእግዚአበሔር /በእግዚአብሔር/ኃይል በሕወት ይኖራል 1ቆሮ 13፣3-5
“የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው” 1ቆሮ 1፣24 -26 ሰዎች ይህንን የእግዚአብሔር ኃይል አላወቁም ነበር “ የእግዚአብሔርን ኃይል አታዉቁም እና ትስታለችሁ” ማቴ 22፣22
5.      አምላክ
ክርስቶስ አምላክ ነው እግዚአብሔር ነው ኢሳይያስ ሕጻን ካለው በኋላ አምላክ ብሎታል “የእግዚአብሔር ስራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጀፐቹ             ኃጢአት  አልሰሩም “ ዮሐ 9፣3 “ያቃልም እግዚአብሔር ነው ዮሐ 1፣1 ሥጋ የለበሰው ሕጻን የተበለው እርሱ ነው እርሱ የሁሉም ፈጣሪ ነው ፡፡ “ሁሉ በእርሱ ሆነ ያለ እርሱ ምንም ምን የሆነ “ዮሐ 1፣3 “ቃል ሥጋ ሆነ “ ዮሐ 1፣14 ሥጋ ሆነ ማለት ሰው ሆነ ተወለደ ማለት ነው “ጌታዬና አምላኬ “ ዮሐ20”እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሳ “መዝ 77፣65 “እግዚአብሔር በእልልታ አረገ”መዝ 46፣5 የሚሉት የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ይመሰክራሉ፡፡እሳይያስም አምላክ ያለው የወረደው የተወለደው ህጻን የተባለው ያረገው ክርስቶስ ነው፡፡ ፈጣሪነቱ “በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን”ኤፌ 2፣20 ፈጣሪ ካልሆነ ሊፈጥር ይችላልን ?”በሰማይም  በምድርም ያሉ ለእርሱ  በእርሱ ተፈጥረዋል” ቆላ 1፣16 “በስጋ ጠተገለጠ በመንፈስም የጸደቀ (የባህርይ አምላክነቱ የታወቀ) ለመላእክት የታየ ለአህዛብ የተሰበከ በዓለም  የታመነ በክብር ያረገ” 1ጢሞ3፣16 የሚሉት አምላክነቱን ሰው መሆኑን መገለጡን መወለዱን መታመሙን በክብር ማረጉን ያሳየናል ስለዚህ ኢሳይያስ ሕጻን  አለው የባሕርይ አምላክ ነውና፡፡
6.      የዘላዓለም አባት
ክርስቶስ አምላካችን ነው ፡፡ አባታችን በፈጣሪነቱ አምላካችን በቸርነቱ አባታችን ነው የመጀመሪያ አባታችን አዳም ለዉድቀታችን ምክንያት ሲሆን ሁለተኛው አባታችን ክርስቶስ አነሳን ስለዚህ አባት ልዩ መሆኑን እንገነዘባለን ፡፡የሥጋዊ አባት በሥጋ ይወልዳል በበወተት በፍትፍ ያሳድጋል የሚያልፍ ርስት አዉርሶ ይሞታል ክርስቶስ ግን ሲወልደን በርቀት ሲያሳድገን በስጋውና በደሙ የሚያወርሰንም የማታልፈዉን መንግሥት ነው ፡፡የዘላለም አባት አባት አለው፡፡ ይህንን እርሱ ባለቤቱ አጽድቆታል “እናንተስ በምትጸልዩበት ጊዜ እንዲህ በሉ በሰማያት የምትኖር አባታችን”ማቴ 6፣9
“ሀግነ ቀዳማየ አበ ዘውእቱ አዳም ወቦቱ ማሰነ ወተለዉነ አበ ዓለም ሀዲስ””የጠፋንበት የመጀመሪያ አባታችን አዳምን ተዉን አዲስ የዓለም አባት ከርስቶስን ተከተለልን ሃይ.አበ ስለዚህ አባት ብሎታል አሳይያስ፡፡
7.      የሰላም አለቃ
ሰላምን በመወለዱ የመሠረተ ያጸና እርሱ ነውና የሰላም አለቃ አለው “በተወለደ ጊዜ ሕጻን በሆነበት ሰዓት ከመላእክት የተሰማው የምስጋና ድምጽ ይኸው ኢሳይያስ ያለው ነው
“ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብዕ””በሰማያት ለእግዚአብሔር ምስጋና ሠላም በምድር ለሰው ልጆች “ሉቃ 2፣1 ህዝብና አህዛብን በምስጋጋና በሃይማኖት አንደ ያደረገ እርሱ ነውና የሰላም አለቃ ብሎታል በዓለም ሁሉን ያስተባበረ ሰላም ተገኝቶ አያውቅም አንዱ ሰላም ሲያገኝ ሌላው ሰላም ያጣል ከርስቶስ ግን ሰላምን ለሁሉም በአንድ ጊዜ የሰተ የሚሰጥ ነውና የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል፡፡ ሰላምን የሚሰጥ የሚይዝ ማለት “ወሀቤ ሰላም መድኃኔዓለም “ መጠሪያው ሰላም ሰጪ ተብሎ ነው ፡፡
“ሰላሜን እሰተሰጣችኋለሁ እኔ የምሰታችሁ ሰላም ዓለም አንደሚሰጣችሁ ኤይደለም “ዮሐ 14፣27 “ሰላም ለሁላችሁ ሁን “ ብሎ ሰላምን ለሁሉ የሰጠ እርሱ ብቻ ነው ዮሐ 20፣26 በክርስቶስ ልደት ዓለም ያጣውን ሰላም አግኝቷል፡፡
ይቆየን



እሑድ 13 ሴፕቴምበር 2015

“ በዚህች ዓመት ደግሞ ተዋት ” ሉቃ.13÷6-9


ጌታችንና መድኃኒታችን ፈጣሪያችንና አምላካችን እግዚአብሔር ወልድ /ኢየሱስ ክርስቶስ/ በመዋዕለ ሥጋዌው በምሳሌ አድርጐ ወንጌልን አስተምሯል፡፡ በምሳሌ ማስተማር ሊተላለፍ የተፈለገውን መልእክት ሲያስተላልፉት ምግብን በጣፈጠ መረቅ ፈትፍቶ እንደ ማጉረስ ያህል ይሆናልና፤ እንዲሁም አንድ መልእከት በምሳሌ ጣፍጦ በቋንቋ ዘይቤ ተውቦ ሲቀርብ ምሥጢሩ ልብን   ይማርካል፡፡ ስለዚህ የሰው አእምሮ በሃይማኖት ልጓም ተስቦ ለምግባረ ጽድቅ እንዲዘጋጅ ጌታችን ለነጋዴው በወርቅ በዕንቁ፣ ለገበሬው በእርሻ በዘር፣ ለባልትና ባለሙያዎች በእርሾ በቡሆ፣…..ወዘተ እየመሰለ ያስተምር ነበር፡፡ማቴ.4÷30፡፡

እኛም ጌታ በምሳሌ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል ለወቅቱ የሚስማማውን  መርጠን እንመለከታለን በሉቃ.13÷6-9 ላይ ይህንንም ምሳሌ መሰለለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት አጠገብ የተተከለች በለስ ነበረች ግን ፍሬ ሊፈልግባት ቢመጣ ምንም አላገኘም፡፡ ስለዚህ የወይን አትክልት ጠባቂዋን እነሆ ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁምና ቁረጣት፤ ስለምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳሉቁላለች? አለው፡፡እርሱ ግን መልሶ ጌታሆይ ዙሪያዋን እስክኮተኩትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚህች ዓመት ደግሞ ተዋት፡፡  ወደፊት ግን ብታፈራ ደህናነው፤ ያለዚያ ግን ትቆርጣታለህ አለው፡፡ ተብሎ ተጽፏል፡፡

ይህ ከላይ የተገለጸው ምሳሌ በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ሲተረጐም  /ሲመሰጠር/ እንዲህ ነው፤ የወይን አትክልት የተባለች ኢየሩሳሌም ናት፣ አንድ ሰው የተባለ እግዚአብሔር ነው፣ በለስ የተባሉ ደግሞ ቤተእስራኤል ናቸው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስእግዚአብሔር ለዘለዓለም አይራብም ይላል ኢሳ.46÷25፡፡ ራሱ ጌታችንምየእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው፡፡ ብሏል ዮሐ.4÷35 ፡፡ ስለዚህ ሰማያዊያን መላእክትን እንዳይራቡ ያደረገ አምላክ እስራኤል ዘሥጋን ገበሬ በማያርስበት ዘር በሌለበት ዝናብ በማይጥልበት ምድረ በዳ መና ከሰማይ አውርዶ የመገበ ጌታ ተራበ ሲባል ያስገርማል! ግን ፍጹም አምላክ እንደ መሆኑ ፍጹም ሰው ሆኗልና አልተራበም አንልም፤ በሥጋ ተርቧልና የዕፀበለስ ፍሬን ፈለገ፡፡

ይኸውም የበለስ ውክልና ከተሰጣቸው ቤተ እስራኤል የሃይማኖትና የምግባር ፍሬን እንደፈለገ ያመለክታል፡፡በለስ ዘይቤ ቤተ እስራኤል እሙንቱ ተብሏልና እግዚአብሔር አምላክ በብሉይ ኪዳን በቅዱሳን ነቢያት አድሮ የሃይማኖት  /የምግባር/ ፍሬ ባገኝባቸው ብሎ ወደ እስራኤል ሔደ፤ ግን ምንም አላገኘም፡፡ እንዲያውም ሕዝቡ ቅዱሳን ነቢያትን በመጋዝ እየሰነጠቁ፣ በምሳር እየፈለጡ በማጥፋት ከዘመን ዘመን ወደ ተለያየ አዳዲስ ባዕድ አምልኮአቸው ሲገቡ አየ፡፡ ስለዚህ የበለስዋን ጠባቂሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም ፍሬ አላገኘሁባትምና ቁረጣትአለው፡፡ ሦስት ዓመት ያለው ዘመነ መሳፍንት፣ ዘመነ ነገሥታትና ዘመነ ካህናትን ነው፡፡ በዚህን ጊዜ የወይን ጠባቂዋ የተባለ መጋቤ ብሉይ ቅዱስ ሚካኤልተራድቼ ሥራ እስካሠራቸው ድረስ የዘንድሮ ይቅር በላቸው እያለ መለመኑን ያጠይቃል፡፡

አንድም ሰው የተባለ አብ ቢሉ በልጁ ህልው ሆኖ፣ ወልድ ቢሉ ሰው ሆኖ ሃይማኖት፣ ምግባር ፍለጋ ወደ እስራኤል ሄደ፡፡ ሦስት ዓመት በመዋዕለ ስብከቱ እየተመላለሰ ሲያስተምራቸውም ምንም ፍሬ አላፈሩምናይህችን ዕፀበለስ ቁረጣት አለው፡፡ መጋቤ ሐዲስ ቅዱስ ገብርኤል ግንተራድቼ ሥራ እስካሠራቸው ድረስ ይቅር በላቸው፡፡ ብሎ ለመነ የጌታን ትምህርት ያልተቀበሉ አይሁድ ግን የንስሐ ንፍሬ ለማፍራት በጄ የሚሉ አልሆኑም፡፡ በአንደበታቸው የአብርሃም ልጆችነን ይላሉ፤ ነገር ግን የአብርሃምን ሥራ ሊሠሩ አልቻሉም፡፡  ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል ልቡግን ከእኔ የራቀ ነው እንዲል፡፡

ስለዚህ ጌታ ከዕፀ በለሷ ዛፍ ምንም የሚበላ ፍሬ ስላላገኘ ረገማት፡፡ አንድም ጌታችን የፈለገውን ባለማግኘቱ ጉባኤ አይሁድን ረገመ፡፡  በአንጻረ በለስ ረገማ ለኃጢአት እንዲል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለዚህ ጉዳይ እስራኤል ከበረከት ይልቅ እርግማን እንዳገኛቸው አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ጸጋ እንዳገኙ ሲገልጽአሕዛብ በእግዚአብሔር ቸርነት አበባ ሰበሰቡ፤ በአይሁድ ዘንድ ግን እሾህ ተረፈ፡፡ ይኸውም የሃይማኖት ጉድለት ነው፡፡ብሏል፡፡

ዛሬም ገበሬ ዘርን ዘርቶ አርሞና ኮትኩቶ ከአሳደገ በኋላ የድካሙን ፍሬ እንደ ሚጠብቅ ሁሉ፤ እግዚአብሔር አምላካችንም በድንቅ መግቦቱ ከአሳደገን ልጆቹ የምግባርና የሃይማኖት ፍሬን ይፈልግብናል፡፡ ግን ጌታ ወደ በለስ ሕይወታችን ቢመጣ ምን ያገኝ ይሆን?  ፍሬ ወይስ ቅጠል? የእግዚአብሔር ቃል ግን ለንስሐ የሚገባውን ፍሬ እንድናፈራ ያዘናልና መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዳይደክም፣ እንዳይጠወልግ፣ እንዳይደርቅና አላስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ወደ እሳት እንዳይጣል የንስሐን ፍሬ ልናፈራ ይገባናል፡፡ ሕይወት ያለ ንስሓ ክንፍ እንደ ሌላት ወፍ ናትና፡፡

በንስሓ ወደ እግዚአብሔር የሚመለሱ ሰዎች ግን ይቅርታን /ምሕረትን/ ያገኛሉ፡፡ እግዚአብሔር የሚመለከተው ያለፈ ማንነታችንን ሳይሆን የዛሬውንና የወደፊቱን ሕይወታችንን ነውና፡፡ ቅዱስ ያሬድእግዚአብሔር ኃጢአታችንን በማሰብ እንጠፋ ዘንድ ከቶ አልተወንም ቸር አምላክ ነውና እንዲል፡፡አዎ! እኛ በንስሓ ከተመለስን አምላካችን በኃጢአታችን ላይ አያስኬደንም፤ እርሱ የኃጢአታችንን አድራሻ ክረምት በፈለቀው ባሕር ውስጥ ይጥለዋልና፡፡ሚክ.7÷18፡፡

እኛ ሰዎች ልብ ካልን በአዲሱ የዘመን መለወጫ ከተፈጥሮ እንኳ ብዙ ነገር መማር እንችላለን፡፡ አዝርእት፣ እፅዋት፣ ታድሰው፣ ቅጠላቸው ለምልሞ በአበባ ተንቆጥቁጠው እናያለን፡፡ ጋራ ሸንተረሩ አረንጓዴ ለብሶ፣ አፍላጋት በየቦታው እየተንፎለፎሉ፤ አዕዋፍ በዝማሬ፣ እንስሳት በቡረቃ ሰማይ ምድሩን ልዩ ያደርጉታል፡፡ ታዲያ ግዑዛኑ ፍጥረታት ጽጌ መዓዛቸውን የአዲስ ዓመት መሥዋዕት አድርገው ሲያቀርቡ እኛስ ምን ይዘናል?

ሰው ሠራሽ ሆኖ መዓዛ የሌለውን፣ ፍሬ የማያፈራውንና አበባ መሰሉን ሳይሆን፣ እግዚአብሔር የፈጠረውን፣ ያለመለመውንና አብቦ መልካም መዓዛ የሚሰጠውን የተፈጥሮ አበባን እንሁን፡፡ ያንጊዜ ዝንቦች ሳይሆኑ ንቦች ማርን ለማዘጋጀት ይቀስሙናል፡፡ ስለዚህ በሃይማኖት ብቻ ያይደለ በምግባርም እናብብ፡፡ ያን ጊዜ ከዘማሪው ክቡር ዳዊት ጋርበቸርነትህ ዓመታትን ታቀዳጃለህ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል የምድረ በዳ ተራራሮችም ይረካሉ ብለን ለመዘመር እንበቃለን ፡፡ መዝ.64÷11-13፡፡

በአጠቃላይ አዲስ ዘመን የአምላክ ስጦታ /በረከት/ ነው፡፡ ስለዚህ በምድር ላይ የሚኖር ማንኛውም ሰው ዘመኑ በፈጣሪ ምልጣን የተያዘና የተገደበ ነው፡፡ቅዱስ ዳዊትአቤቱ እኛ አፈር እንደሆንን አስብ፤ ሰው ዘመኑ እንደ ሣር ነው፡፡ እንደ ዱር አበባም ያብባል ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ግን ያልፋል በማለት ሰው ካደገ በኋላ በሕመም ፀሐይነት ይደርቅና በሞት ነፋስነት ይወሰዳል፡፡ ባለፈው ዓመት ብዙዎች ወደ ሞት መንደር ደርሰዋል፤ እኛም እንደ ነርሱ መንገደኞች መሆናችንን እንርሳ፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም በበኩሉሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን የእግዚአብሔር ቃል ግን ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል በማለት የሰው ሁሉ ክብሩ ሥጋዊ ሕይወቱና ተድላ ደስታው አንድ ጊዜ፣ አንድ ወቅት ለምልሞና አምሮ የሚታይ ሆኖ ሳለ ያው ደግሞ ሳይቆይ የሚጠፋ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ኢሳ.40÷8፡፡ ስለዚህ በአዲሱ ዘመን ራሳቸውን ለከፍተኛ ግብ የሚያዘጋጁ ሁሉ ወደ ተቀደሰ መንፈሳዊ ሕይወት ሊሸጋገሩ ይገባል፡፡ ከእግዚአብሔር የተሰጠን እድሜም የአጭር ጊዜ እንግዳ መሆናችንን ስለሚያስገነዝበን የምንሸኘውም እንዲሁ ባልታወቀ ጊዜው ስጥ መሆኑን በመረዳት እውነተኛ ሃሳባችንና ሥራችንን ለተተኪው ትውልድ የማይረሳ አስመስጋኝ ቅርስ መሆን አለበት ፡፡

እንዲህ ዓይነቱ መልካምነት ደግሞ ለክርስቲያን በአዲሱ ዘመን እንደ ሎተሪ ዕጣ የሚደርሰው ሳይሆን ራሱ ፈልጐ የሚሆነው ነው፡፡ ስለዚህ ይልቁንም በአሁኑ ዘመን በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው ሁሉ ፍጻሜ እያገኘ ባለበት ዘመን ፍቅር በጠፋበት ዘመን አብዛኛው ሕዝብ ለማይረባ ነገር ብሎ ደገኛ ሃይማኖቱን እየለቀቀ ወደ አልባሌ ቦታ ሲገባ የሕይወት ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ እኛ በአዲሱ ዓመት የሕይወት ለውጥን ካሳየን የእግዚአብሔር ጸጋ በውስጣችን ሥራውን በመጀመር በአንድ ሰንሰለት ላይ በርካታ የሕይወት ለውጥን ያመጣልናል፡፡ ይህ የሕይወት ለውጥ በአዲሱ ዘመን ውስጥ ለመኖሩ ተግባራዊ መለኪያው ደግሞ ቀጣይነቱ፣ ፍጹም ተጋድሎውና ግልጽ መሆኑ ነውና ራሳችንን እንመርምር፡፡ 1ጢሞ.4÷7፡፡ የዚያች የወይን ጠባቂ  ወደ ፊት ብታፈራ ደህና ነው ያለ በለዚያ ግን ትቆርጣታለህ እንዳለ ለነፍሳችን አንድ ነገር ሳንይዝ፣ ዘመናችን እንዳያረጅና እንዳይቆረጥ ዛሬ ለበጐ ሥራ እነነሣ፡፡ መጥመቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አሁንም ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጧል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል  ይላልና፡፡ ማቴ.3÷10  እነሆ ! ዛሬ ግን እንደ እግዚአብሔር ቸርነት አሮጌውን ዓመት አሳልፈን ለአዲሱ ዓመት በቅተናል፡፡ ስለዚህ አዲሱን ዓመት በመንፈሳዊ ሕይወታችን ጐልምሰን ፣ ሁላችንም ለተቀደሰ ዓላማ ተሰልፈን፣ ከክፉ ምግባራችንም ተመልሰን የምንቀደስበት የምንባረክበት የሰላም፣ የጤናና የደስታ ዘመን ያድርግልን አሜን!!







የኮ/ደ/ብ/ቅ/ሥላሴ ቤ/ክ አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ሃይለ ማርያም መንገሻ የአውደ ዓመት መልካም ምኞትና መልዕ


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

አዲሱ አመት የሰላም፣የፍቅር፣ የዕውቀት፣ የልማት፣ የእድገት ፣የትምርህት፣ የስራ፣ የብልጽግና፣የጤና ዘመን እንዲያደርግልን እግዚአብሔር እየተመኘሁ፡፡


የአባቶቻችን የቀናች ሃይማኖት
ቅድመ አለም ከነበረው ዓለምን ከፈጠረው እግዚአብሔር አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ከሦስት አካል አንዱ እግዚአብሔር ወልድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስን ነስቶ ተወለደ፡፡
ይህ ቅድመ አለም የነበረው ከድንግል ማርያም የተወለደው እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁለት አካል አንድ አካል ከሁለት ባህርይ አንድ ባህርይ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነው ብሎ በምስጢረ ተዋህዶ ማመን ኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ እምነት ነው፡፡
ቀዳማዊ ደሐራዊ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከባህርይ አባቱ ከአብ ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ አለም ሳይፈጠር የነበረ ሲሆን ያለ እርሱም ምንም ምን አልተፈጠረም እርሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ዩሐ.፩፣ ፩-፲
ቃለ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ያለዘርዐ ብእሲ ሲወለድ የቅድስት ድንግል ማርያም ማህተመ ድንግልና አልተለወጠም እመቤታችን ድንግል ማርያም ድንግል ወእም ድንግል ሳለች እናት እናት ሳለች ድንግል ናት፡፡
ስለ ምስጢረ ድህነት ትምህርት ሲነገር የምስጢረ ድህነት መነሻዋ ድንግል ማርያም ናት ይኸውም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ያዳነው ከድንግል ማርያም በነሳው ሥጋ የሰው ዘርን በመውደዱ እስከ ሞት ድረስ ባደረገው ካሳ ነው፡፡
ቅዱሳን አበው ሐዋርያት ያስተማሩት የቤተክርስትያን ትምህርት ከሁሉ በላይ የሆነ ሊከለስ ሊለወጥ የማይችል አማናዊ ቃለ እግዚአብሔር ኦርቶዶክሳዊ እምነት ይህ ነው፡፡
ይህ ኦርቶዶክሳዊ እምነት ከራሱ ከፈጣሪያችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘ በቅዱሳን አበው ሐዋርያት ከአለም መካከል እስከ አለም ዳርቻ የተሰበከ በሐዋርያት አበው በሦስት መቶ አስራ ስምንቱ አበው የጸና ኦርቶዶክሳዊ እምነት ነው፡፡
የአባቶቻችን ሐይማኖት የቀናች ናት ርትዕት ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ ተብሎ እንደ ተነገረው “ኢታንትጉ ወኢትወሰኩ እምዘ መሐርናክሙ ” እኛ ካስተማርናችሁ እምነት ሌላ አትጨምሩ አትቀንሱ መልአክ እንኳ ከሰማይ መጥቶ ቢያስተምራችሁ አትቀበሉ ተብሎ ተጽፏል፡፡
ሕገ ሃይማኖት እንደ ስጋዊ ሥርዓት ተለዋዋጭ አይደለም፡፡ሥጋዊ ሥርዓት ከሰው የተገኘ ስለሆነ እንደ ሰዎች ሥልጣኔ ሊያድግ ይችላል ሕገ ሃይማኖት ግን የተገኘ ከእግዚአብሔር ስለሆነ የእግዚአብሔር ቃል ከሁሉ በላይ ከማንኛውም የተራቀቀና የመጠቀ ስልጣኔ በላይ ስለሆነ ሕገ እግዚአብሔር አይለወጥም፡፡ በሕገ ሃይማኖት የጸኑ በትሩፋት የጎለመሱ ኦርቶዶክሳውያን ካህናትና ምእመናን በረድኤተ እግዚአብሔር ተጠብቀው በህጉ ከብረው በጸጋው ተጎብኝተው ይኖራሉ፡፡
                                                    ቆሞስ አባ ሃይለ ማርያም መንገሻ የኮ/ደ/ብ/ቅ/ሥላሴ ቤ/ክ አስተዳዳሪ