ረቡዕ 31 ዲሴምበር 2014

አስደናቂ የክርስቶስ ልደት



v  “በልዑል ዙፋን ላይ ተቀምጦ ያለ እርሱ በበረት ተጣለ፣ ስጋ ሳይሆን የነበረ የማይዳሰስ ወልድ ዋህድ ዘሬ ስጋን በመዋሃድ ተዳሰሰ፣ሃጥያትን ይቅር የሚል ራሱ በጨርቅ ተጠቀለለ” (ሃይማ.አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ)
v  “ኦ ለዝንቱ መንክር ልዑል…”ከህሊናት ሁሉ ለላቀ ለዚህ ድንቅ ምስጥር አድናቆት ይገባል፤ምድራዊት ሴት ሰው የሆነ እግዚአብሔር ቃልን ወለደችው፤ድንግል ፈጣሪዋን ወለደችው፤እርሱም እናቱን ፈጠረ፤ከእርሷም እርሱ የፈጠረውን ስጋ ተዋሐደ በእኛ ባህርይ ተወለደ እርሱም እኛን ስለመውደዱ ፈጠረን በእኛ ባህሪይ ወለደችው ፈጣሪም እንደሆነ ታወቀ፡፡(ቅ.ያዕቆብ ዘስሩግ)
v  “ዳያቢሎስ በልደት ማየት የተሳነውና ያስደነገጠው ብርሃን፤ዳግመኛም በዕለተ አርብ በብርሃን ነጸብራቅ ኃይል የጨለማውን አበጋዝ እውር ያደረገው ይህ ማን ነው፤ወገኖቼን እገዛ ዘንድ ያልተወኝ ይህ ማን ነው? ነገር ግን ተሰጠተውኝ የነበሩት ነፍሳትን ሁሉ ወደሰማይ ያወጣል እንጂ በማለት ፍጹም ሽንፈቱን ገልጾታል፡፡ ”(ትምህርተ ኅቡአትን ተመልከቱ)
v  #ዲያብሎስ በስጋ ከይሲ ተሰውሮ አዳምን ድል በነሳው ጌታ ድግሞ በጥበብ በስጋ ብእሲ ተሰውሮ ዲያብሎስን ድል ነስቶታል;(መቅድመ ወንጌል)
v  “ጌታ ሲወለድ በቤተልሔም ብርሃኑ ሲያበራ ሰይጣን እየተቻኮለ ከሰፈሩ በወጣ ጊዜ ክፉዉ ጭፍራ በጸጥታ ቆሞ ይጠብቀው ነበር፤ራሱም በርሮ ወጣ ወደ ከፍታዎችና ወደ ዝቅታዎችም ሁሉ ፈጠነ በሁሉም ክልሎችና ድንበሮች አለፈ፡፡ከሩቅ ሆኖ ወደ ቤተልሔም አቅጣጫ ተመለከተ አንድ መልኣክም በአስደናቂ ክብር የብርሃንንም ጸዳል ተላብሶ፤እየበረረ ሲዞር ሲመላለስም፤በደስታ ተመልቶ እና እየፈጠነ፤ውብ እና አስደሳች ሆኖ አሳቱ እጅግ እያበራ ከድምፁም ታላቅ ብርሃን እያመነጨ ሲያልፍ አየ፤ሰይጣንም አይቶት በፍርሃት እየራደ ተሸሸገ፡፡”(በቅዱስ ያእቆብ ዘስሩግ ድርሳን)
v  ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ላይ “ትእምርተዋሕዱ ረሰየኪ አብ”አብ የራሱ ምልክት አደረገሽ አለ እርሱ ቅድመ ዓለም ያለ እናት፤አንድም ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው የአንድ ልጅ ምልክት አደረገሽ አለ እሷ ድንግልወእም (ድንግልም እናትም) ስትባል መኖሯ ራሱም አምላክወ ሰብእ (አምላክም ሰውም) ሲባል የመኖሩ፤እርሷም ስትወልደው ማኀተመ ድንግልናዋ አለመለወጡ እርሱም ሰው ሲሆን ባህርየ መለኮቱ ያለመለወጡ ምሳሌነት በማለት ምሳሌነቱትን አስቀምጦል፡፡


ሰኞ 15 ዲሴምበር 2014

ታህሳስ 2007 ባታለማርያም በኮልፌ ደብረብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ

ታህሳስ 2007 ባታለማርያም በኮፌ ደብረብርሃን ቅድስት ላሴ ቤ/ክ

እግዚአብሔር አገልግሎታችን ይቀበልልን!!እንዲህ በደብረ ብርሃን እንዳማረብን ሰማያዊት በሆንችው ነጻ በምታወጣው በደብረ ጽዮን ይሰብሰበን!!!











ሐሙስ 11 ዲሴምበር 2014

“ስእለቴን ይዤ ወደ ቤትህ እገባለሁ” መዝ 65፡13

“ስእለቴን ይዤ ወደ ቤትህ እገባለሁ” መዝ 65፡13
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አባቷ ኢያቄም እናቷ ሐና ይባላሉ፡፡የተወለደችው በእግዚአብሔር ፈቃድ በብስራተ መልአክ ነው፡፡አባትና እናቷ እግዚአብሔርን ልጅ ብትሰጠን ብለው ተስለው ነበር ሦስት ዓመት ሲሆናት ኢያቄም ለሐና ይህች ልጅ አንድ ነገር ብትሆን ከእግዚአብሔር ከልጃችንም ሳንሆን እንዳንቀር ሆዷ ዘመድ ሳይወድ አፏ እህል ሳይለምድ ወስደን እንስጥ ብለው መባ ጨምረው ወደ ቤተመቅደስ ይዘዋት ሄዱ ሊቀ ካህኑ ዘካርያስ ይባላል ደወል መትቶ ሕዝቡን ሰብስቦ የምግቧ ነገርስ? አለ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ፋኑኤል ኅብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ ይዞ ረቦ ታየ፡፡ዘካርያስም ለርሱ የመጣ መስሎት ከእርሱ ሊቀበል ተነሳ ወደ ሰማይም ራቀበት ከእርሱ ቀጥሎ ያለው ሊቀ ካህንም ሊቀበል ሲቀበርብ ራቀበት፡፡ካህናቱም ሕዝቡም በየተራ ቢቀርቡ ራቀባቸው ምን አልባት ለዚህች ብላቴና የመጣ እንደሆነ እንይ አሉ፡፡ሐናን ትተሻት እልፍ በይ አሏት፡፡ትታት እልፍ አለች ድክድክ እያለች እናቷን ስትከተል መልአኩ ፈጥኖ ወርዶ አንድ ክንፉን አንጥፎ አንድ ክንፉን ጋርዶ በሰው ቁመት ልክ ከመሬት ከፍ አድርጎ መግቧት ዐረገ፡፡ ለቀ ካህኑ ዘካርያስ የምግቧ ነገር ከተያዘ ብሎ ከመካነ ደናግል አስገብቶታል፡፡ኅብስተ ሰማያዊ ጽዋዐ ሰማያዊ እየተመገበች መላእክት እየጎበኞት አስራ ሁለት አመት በቤተመቅደስ ኖረች፡፡

1.   ትምህርት
·         ኢያቄምና ሐና ጸሎታቸውና ልመናቸው መሰማቱን “እግዚአብሔር የልመናዪን ድምጽ ሰምቶአልና ወደድኩት” (መዝ114፡1)
·         ስለትን ማክበር
“ተስለህ የማትፈጽም ብትሆን ባትሳል ይሻላል፡፡” (መክ5፡5)
2.   መልእክት

የሰው ልጆችን ልመና የማያስቀር አምላክ የኢያቄምንና የሐናን ጸሎት ሰምቶ የሰጣቸውን አንዲት ልጅ ነቢያት በብዙ ምሳሌ ትንቢት የተናገሩላትን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በገቡት ቃል ኪዳን መሠረት ለልጃቸው ሳይሳሱ በሦስት ዓመቷ ወደ ቤተመቅደስ ይዘዋት ሄዱ፡፡እመቤታችን ቀድስት ድንግል ማርያም ሐርና ወርቅ እየፈተለች ሰማያዊ መና እየተመገበች በንጽሕናና በቅድስና ኖረ፡፡በዚህ ዘመን የምንኖር እኛም እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ዘወትር ከመቅደሱ ሳንለይና በንጽሕናና በቅድስና እንድንኖር የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትና ጸሎት አይለየን አሜን፡፡ 

ዓርብ 21 ኖቬምበር 2014

የማይረሳ ለሊት(ዘጸ12፡42)




 በዚህ ዕለት የሚከበረው በዓል እስራኤል ዘስጋ ለ430 ዓመት በግብጽ ከኖሩ በኋላ በዛሬ ዕለት የወጡበት በዓል ይታሰባል፡፡እስራኤላውያን ወደ ግብጽ ከከነዓን ወጥተው የገቡት
በርሀብ ምክንያት ሲሆን ወንድማቸው ዮሴፍንም አስቀድመው ሸጠውት ነበር፡፡

ከከነዓን ተሰደው በረሀብ ምክንያት ወደ ግብስ 70 ቤተሰብ ሆነውገቡ፡፡ከብዙ ዘመን በ|ላ ዮሴፍን የማያውቅ ፈርዖን ተነሳ፡፡እስራኤል ከእኛ ይልቅ በዝተዋል ጠላት ቢነሳብን ተደርበው ያጠፉናል
ብሎ መከራና አገዛዘ አጸኑባቸው መከራ እየተቀበሉ ሲሰቃዩ ኖሩ ወንድ ልጆች ሲወለዱ በአዋላጆቻቸው እንዲገደሉ ትዕዛዝ ተሰጠ ራሔል የምትባል ዕብራዊት ባሏ ሮቤል ሞቶባት የባሏን ሥራ
ደርበሽ ሥሪ ተብላ ጭቃ ስትረግጥ ምጥ ያዛት ጥቂት ልረፍ አለች የሚሰራው ግብጻዊ እርገጪ ብሎ አስገደዳት በማህፀኗ የነበሩት መንታ ሕፃናት ከእግሮ ስር ወደቁ የልጅ ደም ግንብ ያጠነክራል
ብሎ ከጭቃው ጋር እርገጫቸው አላት እንባዋን ወደ ሰማይ ረጨች #ቃል ተሰማዐ በራማ ወሰቆቃው ወገዓር ራሄል እንዘ ትበኪ በእንተ ውሉዳ ወአበየት ተናዝዞ ወነጊፈ ለህ; (ኤር 31፡15፤ማቴ 2፡17)

ከዚህ በ|ላ እግዚአብሔር ለሙሴ ፈርዖንን ሕዝቤን ልቀቅ ይልሃል በለው፡፡ ፈርኦንም መልሶ እስራኤልን እለቅ ዘንድ እግዚአብሔር ማንው? በማለት የፈርዖን ልብ ደንድኖ አልሰማም አለ በዘጠኝ
መቅሰፍት በአስረኛው ሞተ በኩር ግብጻውያንን መታቸው እግዚአብሔርም ለሙሴ እንግዲህ አለው ጫማችሁን በእግራችሁ በትራችሁንም በእጃችሁ  አድርጋችሁ እንዲህ በሉት የእግዚአብሔር ፋሲጋ
ነው፡፡እኔም በዛች ሌሊት በግብጽ አገር ከሰው አስከ እንስሳ ድረስ በኩርን ሁሉ እገድላለሁ በግብጽ አማልክት ሁሉ እፈርድባች|ለሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ደሙም ምልክት ይሆናች|ል፡፡(ዘጸ 11፡11)

እግዚአብሔርም ሙሴን #ሕዝቡን ከባርነት ከግብጽ የወጣችሁበትን ይህንን ቀን አስቡ; አለው፡፡(ዘጸ 13፡1) እንዲህም ሆነ እኩለ ሌሊት በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር ከተቀመጠው ከፈርዖን በኩር ጀምሮ
በግዞት እስካሉት እስከ ምርኮኞች ድረስ የግብጻውያኑን በኩር መታ፡፡ህዝቡንም ነጻ አወጣ፡፡

v  ትምሕር
·         ሁሉን የሚያደርግ እግዚአብሔር በቻ መሆኑን ማወቅ
#እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል እናንተም ዝም ትለላችሁ;(ዘጸ 14፡14)
·         የነጻነት ቀን መዘከር
#ከባርነት የወጣችሁትን ይህን ቀን አስቡ;(ዘጸ 13፡1)
·         ድል ከእግዚአብሔር መሆኑን
#እግዚአብሔር ተዋጊ ነው ስሙም እግዚአብሔር ነው; (ዘጸ 15፡3)
·         የግብጻውያን አማልክት የተዋረዱበት
·         የአግዚአብሔር አስደናቂ ተአምር የታየበት (ዘጸ 14፡14)
·         እስራኤላዊያን የተደሰቱበት (ዘጸ 15፡2)
v  መልእክት
ከ430 ዓመታት በ|ላ እስራኤላውያን ከፈርዖን  የባርነት አገዛዝ ወጥተዋል፡፡ እኛም በዘመናችን ከዲያብሎስ ባርነት መላቀቅ ይገባናል #በነፃነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻ አውጥቶናልና; (ገላ 5፡1)
እኛም የማንረሳው ሌሊት ከሞት ውርደት የተነሣንበት ሌሊት ቃሉን በምስጋና ተሞልተን ስንዘምር ያደርንበትን ሌሊት ልንረሳው አይገባንም፡፡
                       የእግዚአብሔር ቸርነት አይለየን አሜን!!!

ማክሰኞ 7 ኦክቶበር 2014

ማኅሌተ ጽጌ



ማኅሌተ ጽጌ፤ ምንጩ ትርጉሙ መልእክቱ 

        ይህ ድርሰት በማንኛውም ጊዜ የሚጸለይ ቢሆንም በተለየ ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውለው ከመስከረም 26 እስከ ኅዳር 5 ቀን ድረስ ባለው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የስደት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅት በየሳምንቱ እሑድ ሌሊት በሙሉ የእመቤታችንን ከልጇ ጋር ወደ ግብፅ መሰደድና መንከራተት እያሰቡ የሚደረስ ምሥጋናና ጸሎት ነው፡፡
             በሀገራችን የመስከረምና የጥቅምት ወራት የአበባ ወራት /ዘመነ ጽጌ/ ናቸው፡፡ ይህም ወቅት ተራሮች በአበባ የሚያጌጡበትና ለዓይን ማራኪ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህም ዘመን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ስለ ልብስስ ስለምን ትጨነቃላችሁ) የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፡፡ አይደክሙም፣ አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞንስ ስንኳ በክብሩ ሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም፡፡ እግዚአብሔርን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጐደላችሁ እናንተንማ ይልቁን እንዴት እንግዲህ ምን እንበላለን ምንስ እንጠጣለን) ምንስ እንለብሳለን) ብላችሁ አትጨነቁ ...» /ማቴ.5÷28-33/ በማለት የተናገረውን ቃል በማሰብ መጨነቅ የሚገባን መንግሥተ ሰማያት ለመግባት እንጂ በዚህ ዓለም ስላለው ነገር እንዳልሆነ ተራሮችን በአበባ ያለበሰ አምላክ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረንን እኛን ለኑሮ የሚያስፈልገንን ምግብና ልብስ እንደማይነሳን እያሰብን የምንዘክርበት ወቅት ነው፡፡
                እንዲሁም ክቡር ዳዊት «ተዘከር እግዚኦ ከመ መሬት ንሕነ ወሰብእሰ ከመ ሳዕር መዋዕሊሁ ወከመ ጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ፤ አቤቱ እኛ አፈር እንደሆን አስብ ሰውስ ዘመኑ እንደሣር ነው እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና» /መዝ.1ዐ2÷14-16/ በማለት እንደ ተናገረው የሰው ሕይወት በሣር ይመሰላል፡፡ ሣር አድጐ አብቦ ከዚያ በኋላ ይደርቅና በነፋስ አማካኝነት ያ የረገፈው ሣር እየተነሣ የነበረበት ቦታ ስንኳ እስከማይታወቅ ድረስ ይሆናል፡፡ ሰውም ከአደገ በኋላ በሕማም ፀሐይነት ይደርቅና በሞት ነፋስነት ይወሰዳል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ መቃብር ሲወርድ የነበረበት ቦታ ይዘነጋል፡፡ ስለዚህ ዘመነ ጽጌ ሰው ዘመኑ እንደ አበባ በቶሎ የሚረግፍ መሆኑን በማሰብ ይህ ዘመን ሳያልፍ መልካም ሥራ ለመሥራት ትንሣኤ ኅሊና የሚነሣበት ጊዜ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለዘመነ ጽጌ የሠራው ድጓም ይህንኑ የሰውን ዘመን አጭርነት የሕይወቱን ኢምንትነት በዚህ ሕላዌ የተፈጠረ ሰው በዚህ ዓለም ክፉ ሥራ መሥራት እንደሌለበት ሁልጊዜ በተዘክሮተ ሞት እንዲኖር የሚያስረዳ ነው፡፡
                     በዘመነ ጽጌ ቅዱስ ያሬድ ከደረሰው ድጓ በተጨማሪ ከላይ እንደተጠቀሰው በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣ አባ ጽጌ ድንግል ከዚሁ ዘመን ጋር የተያያዘ ድርሰት ደርሷል፡፡ ይህ ድርሰት በግጥም መልክ የተደረሰ በአብዛኛው አምስት ስንኞች ያሉት ሲሆን ብዛቱም 15ዐ ያክል ነው፡፡ ይህም ድርሰት «ማኅሌተ ጽጌ» በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ፍሬ ከአበባ አበባም ከፍሬ እንደሚገኘው ሁሉ ማኅሌተ ጽጌም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን መድኃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአበባና በፍሬ እየመሰለ የሚያስረዳ ድርሰት ነው፡፡ እርሷን በአበባ ሲመስል ልጇን በፍሬ እርሷን በፍሬ ሲመስል ደግሞ ልጇን በአበባ እየመሰለ ይናገራል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ «ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ ወየዓርግ ጽጌ እምጉንዱ፤ ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፤ ከሥሩም ቁጥቋጦ ያፈራል»  /ኢሳ.11÷1/ ብሎ ከእሴይ ዘር የምትገኘውን እመቤታችንን በበትር ከርሷ የሚገኘውን ክርስቶስን ደግሞ በጽጌ መስሎ ትንቢቱን ተናግሯል፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም ድርሰቱን በዚሁ አንጻር በመቀመር እያንዳንዱን መልክዕ እመቤታችንንና ልጇን አስተባብሮ በጽጌና በፍሬ በመመሰል የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ በምሥጢር በታሪክ፣ በጸሎትና በመሳሰለው መልክ ድንቅ በሆነና በተዋበ ሁኔታ አዋሕዶ ደርሶታል፡፡
                     እመቤታችን ጣዕሟንና ፍቅሯን እንዲሁም ምስጋናዋን ሲናፍቁ የነበሩትን ቅዱስ ኤፍሬምንና አባ ሕርያቆስን ውዳሴዋንና ቅዳሴዋን እንደገለጸችላቸው ለፍቅሯ ሲሳሳ ለነበረው ለአባ ጽጌ ድንግል ደግሞ ይህንን ማኅሌተ ጽጌን እንዲደርስ አድርጋዋለች፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ማኅሌተ ጽጌ በመልክዕ አደራረስ ሥርዓት የተደረሰ ሲሆን ይህንንም ለመመልከት እንዲያመች በሚከተሉት ክፍሎች ከፋፍሎ ማቅረብ ይቻላል፡፡
1. ጸሎት
            በዚህ አገባብ ጸሎት ስንል በተለየ ሁኔታ ጸሎትነቱ የጐላውን ለማየት እንጂ ድርሰቱ በሙሉ ጸሎት ነው፡፡ ሌሎቹንም እንዲሁ ታሪክ፣ ተግሳጽ፣ ምሥጢር ተብለው መከፈላቸው በበዛውና በጐላው ለመግለጽ ነው እንጂ ሁሉም በሁሉ አለ፡፡ በጸሎትነታቸው ጐልተው ከሚታዩት ውስጥ የተወሰኑትን እንመለከታለን፡፡

1.1.  አንብርኒ ማርያም ውስተ ልብኪ ከመ ሕልቀት፣
ወከመ ማዕተብ ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት፣
በእንተ ርስሐትየሰ ኢትመንንኒ ንግሥት፣
እስመ ወሀብኩ ንብረትየ ለፍቅርኪ ሞት፣
ዘአሰገርዎሙ ለሰማዕት በጽጌሁ ሕይወት፡፡
              ጠቢቡ ሰሎሞን «የምእመናንንና የክርስቶስን ነገር በምሥጢር በተናገረበት በመኃልይ መጽሐፉ «እንደ ማኅተም በልብህ እንደ ማኅተም በክንድህ አኑረኝ» /መኃ.9÷6/ ይላል፡፡ ይኸውም የምእመናንንና የክርስቶስን አንድነት የሚገልጽ ነው፡፡ «አንብርኒ ማርያም ውስተ ልብኪ ከመ ሕልቀት፤ ወከመ ማዕተብ ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት» ማለቱ እመቤታችንን እንደ ማኅተም በልብሽ አኑሪኝ በማለት በእናትነትሽ፣ በአማላጅነትሽ አትርሽኝ ካለ በኋላ «በእንተ ርስሐትየሰ ኢትመንኒ ንግሥት» ይላል፡፡ ይኸም ማለት አትርሽኝ በልብሽ አኑሪኝ ብዬ የምለምንሽ አንቺ እንዳትረሽኝ የሚያደርግ መልካም ሥራ ኖሮኝ አይደለም፡፡ ስለዚህ በሰውነቴ ክፋት ምክንያት በኃጢ አቴና በወራዳነቴ ምክንያት እኔን ከማሰብ ከልቡናሽ አታውጪኝ በማለት እመቤታችን በርኅሩኅ ልቧ «መሐር ወልድየ ወተዘከር ኪዳንየ» እያለች እንድታዘክረን የሚያሳስብ ጸሎት ነው፡፡

ሶበ አተቦ ለማይ በቅዳሴኪ እንዘ ይጼሊ፣
ረሰዮ ኅብስተ ጽጌ ሃይማኖት ሳሙኤል ዘሐቅለ ዋሊ፣
ምሕረተ ወፍትሐ ለተአምርኪ አኀሊ፣
ሥረዪ ኃጢአትየ ወእጸብየ አቅልሊ፣
እስመ ኩሎ ገቢረ ማርያም ትክሊ፡፡
            አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ቅዳሴ ማርያምን እየደገሙ ውኃው በተአምራት ኅብስት ይሆንላቸው ነበር፡፡ ይህን ተአምር ከአደነቀ በኋላ «ማርያም ሆይ ሁሉን ማድረግ ትችያለሽና ኃጢአቴን አስተስርይልኝ» ይላል፡፡ ጌታችን «እውነት እላችኋለሁ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም» /ማቴ.17÷1/ በማለት ላመነ የሚሣነው ነገር እንደሌለ ተናግሯል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መልአኩ «ትጸንሻለሽ፣ ትወልጃለሽ ...» ብሎ ባበሠራት ጊዜ ይህ እንደምን ይሆንልኛል)  ብላ ስትጠይቅ «ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም» ሲላት በፍጹም እምነት ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ እንደቃልህ ይሁልኝ» በማለት የተቀበለች ናት፡፡ ይህንንም ቅድስት ኤልሳቤጥ መንፈስ ቅዱስን ተመልታ «ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና የታመነች ብፅዕት ናት» /ሉቃ.1÷453 ብላ መስክራለች፡፡ ላመኑ ሁሉ የሚቻል ከሆነ እመቤታችን ግን ቅዱሳን ሁሉ የሚማጸኑትን አምላክ በሥጋ ወልዳ ያስገኘች ስለሆነች ለእርሷ የሚሳናት ነገር የለም፡፡ ስለዚህም ነው ላንቺ የሚሳንሽ ነገር የለምና ኃጢአቴን አስተስርዪልኝ፣ የከበደኝን ሁሉ አቅልይልኝ በማለት የለመነው፡፡

1.2. «ተአምርኪ ማርያም ተሰብከ በኦሪት፣
አመ ተሰነዓውኪ ጳጦስ ምስለ መለኮት፣
ዘርእየኪ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
ጸልልኒ በአዕፁቅኪ ሐመልማላዊት ዕፀት
ሦከ ኃጢአትየ ያውዒ ጽጌኪ እሳት፡፡
              «ማርያም ሆይ ነበልባል ከሐመልማል ተዋሕዶ ሙሴ በደብረ ኮሬብ ባየ ጊዜ ተአምርሽ በኦሪት ተሰበከ ተነገረ፡፡ ምሳሌሽ በሐመልማልና በእሳት አምሳል የታየ ማርያም ሆይ ጽጌ ልጅሽ ኃጢአቴን ያጠፋልኝ ዘንድ በጥላሽ ሥር አስጠጊኝ፡፡
               ሙሴ በምድያም በስደት ሆኖ የአማቱን የዮቶርን በጎች እየጠበቀ ሳለ በኮሬብ ተራራ ድንቅ ራእይ ታየው፡፡ ቁጥቋጦው በእሳት ሲነድ፡፡ ቁጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ፡፡ ዘጸ.3÷3፡፡ ይህ የምሥጢር ተዋሕዶ ተምሳሌታዊ ራእይ ነበር፡፡ ሐመልማል የእመቤታችን ምሳሌ ሲሆን እሳቱ ደግሞ የመለኮት ምሳሌ ነው፡፡ የሐመልማሉ ርጥበት እሳቱን አለማጥፋቱ አምላክ ሰው ሲሆን ከመለኮቱ ክብር ዝቅ ያለማለቱ ምሳሌ ነው፡፡ እሳቱ ደግሞ ሐመልማሉን አለማቃጠሉ መለኮት ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ በተዋሐደ ጊዜ እንዳጸናትና እንዳደረገችው የሚያስረዳ ነው፡፡



             ደራሲው የእመቤታችን ክርስቶስን የማስገኘት ተአምርና የእርሷ የአምላክ እናት መሆን ከጥንት ጀምሮ ሲነገር የኖረ መሆኑን ካስታወሰ በኋላ ጸሎቱን «ጸልልኒ በአዕፁቅኪ ሐመልማላዊት ዕፀት ሦከ ኃጢአትየ ያውኢ ጽጌኪ እሳት» በማለት ያቀርባል፡፡ ይኸም ማለት «ያ ከሐመልማል ጋር ተዋሕዶ የታየው እሳት ጽጌሽ/ ልጅሽ ክርስቶስ/ ኃጢአቴን ያስተስርይልኝ ዘንድ በአንቺ ሐመልማልነት አስጠጊኝ ማለት ነው፡፡
               ዳዊት «በአንቺ የሚኖሩ ሁሉ ደስ ይላቸዋል» /መዝ.8÷ኮ7/ ብሎ እንደተናገረ በእመቤታችን እናትነትና አማላጅነት ጥላ ሥር የሚኖሩ ከልጇ ከክርስቶስ ሥርየተ  ኃጢአትን አግኝተው፣ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ተጐብኝተው ደስተኞች እንደሚሆኑ የተናገረው ትንቢት መፈጸሙን የሚያስረዳ ነው፡፡
2. ታሪክ
            በብሉይና በሐዲስ ኪዳን በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙትን ድርጊቶች እያነሣ የሚሔድና በዚያውም ከታሪኩ ጋር አብሮ ጸሎትና ምሥጢር የያዘ ነው፡፡ ታሪክን ከሚያነሡት መካከል የሚከተሉትን ለአብነት መመልከት ይቻላል፡፡

2.1. «እስከ መነነቶ ሜልኮል ቅድመ ታቦተ ሕግ ከመ ዘፈነ፣
ንጉሠ እስራኤል ኪያኪ ዘጸገየ ስነ፣
ቅድመ ገጸ ሥዕልኪ ድንግል እዘፍን አነ
ዘይሜንን ተአምረኪ ወስብሐተኪ ቁርባነ፣
በአፈ መላእክት ወሰብእ ለይኩን ምኑነ፡፡
              ዳዊት ታቦተ ጽዮንን ከአቢዳራ ቤት ወደ ከተማው ባስመጣ ጊዜ በሙሉ ኃይሉ በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ሲዘምር ሜልኮል ተመልክታ በልብዋ ናቀችው፡፡ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ስላዘነበባት ልጅ ሳትወልድ ሞታለች፡፡ ሳሙ.6÷12-23፡፡ ደራሲውም ይህንን ታሪክ ካስታወሰ በኋላ «ቅድመ ገጸ ሥዕልኪ ድንግል እዘፍን አነ» ዳዊት «ለእመቤታችን ምሳሌ በሆነች በታቦተ ጽዮን ፊት እንደዘመረ እኔም በሥዕልሽ ፊት ላንቺ እዘምራለሁ»፤ «ዘይሜንን ተአምረኪ ወስብሐትኪ ቁርባነ በአፈ መላእክት ወሰብእ ለይኩን ምኑነ ሜልኮል በዳዊት ይቀርብ የነበረውን የታቦተ ጽዮንን ምስጋና በመናቋ እንደተረገመች ያንቺንም ተአምርሽንና ምስጋናሽን የሚንቅ ሁሉ በሰውና በመላእክት አፍ የተረገመ» ይሁን የሚል ነው፡፡ ሜልኮል የምሳሌዋን የታቦተ ጽዮንን ምሥጋና በመናቋ ከተረገመች ዛሬ የአማናዊቷን ታቦተ ጽዮን የእመቤታችንን ምሥጋና የሚንቁና ምሥጋና የሚያቀርቡትን የሚነቅፉ ሰዎች ምን ያኽል የተረገሙ ይሆኑ) እነዚህም «በድፍረትና በመናቅም በጻድቅ ላይ የሚናገሩ የሽንገላ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ» /መዝ.3ዐ ÷18/ ባለው ርግማን የተረገሙ ናቸው፡፡
2.2. እንበይነ አውሎጊስ ለዳንኤል አመ አርአዮ ስቅለተ፣
ከመ እገሪሁ ሰዓምኪ ወሰአልኪዮ ምሕረተ፣
ለተአምረ ሣህል ወልድኪ በእንተ ፍቅረ ሰብእ ዘሞተ፣
እንዘ ታዘክሪዮ ድንግል ይምሐረኒ ሊተ፣
ከናፍሪሁ ጽጌ አንኂ ስዕመተ፡፡
                  አውሎጊስ የሚባል የወፍጮ ድንጋይ እየጠረበ በመሸጥ ከዚያ በሚያገኘው ትንሽ ገቢ የሚተዳደር ደኃ ሰው ነበር፡፡ የሚያኘውንም ገንዘብ ለራሱ ትንሽ ለዕለት ኑሮው ካስቀረበ በኋላ ከርሱ የባሰባቸው ችግረኞችን እየረዳ ይኖር ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን በዚህ ግብር ሳለ አባ ዳንኤል የሚባል ባሕታዊ ያየዋል፡፡ ይህም ባሕታዊ አውሎጊስ በዚህ በድህነት ኑሮው እንደዚህ ድሆችን የሚረዳ ከሆነ ብዙ ገንዘብማ ቢያገኝ ምን ያክል ብዙ ሰው በረዳና መልካም ሥራ በሠራ ነበር» ብሎ እግዚአብሔር ለዚህ ሰው ብዙ ሀብት እንዲሰጠው ሱባኤ ያዘ፡፡ እግዚአብሔርም ሀብት ለዚህ ሰው /ለአውሎጊስ/ እንደማይጠቅመው ቢነግረውም አባ ዳንኤል በራሱ ሀሳብ ብቻ በመጓዝ ሀብቱን እንዲሰጠው አጥብቆ ስለተማፀነ እንደለመነው ሊያደርግለት ጸሎቱን ተቀበለ፡፡ ከዚህ በኋላ አውሎጊስ እንደልማዱ ድንጋይ ሲቆፍር በማሰሮ የተቀበረ ወርቅ አገኘ፡፡ ወርቁን ወስዶ ለንጉሡ ሰጠ፡፡ ንጉሡ ወርቅ ሲያገኝ ለራሱ ሳያደርግ ለንጉሥ የሚያመጣ ሰው ምን ያክል ታማኝ ቢሆን ነው ብሎ በዚያው በቤተ መንግሥቱ እንደራሴ አድርጎ ሾመው፡፡ አውሎጊስ ከተሾመ በኋላ አጃቢው ክብሩና ሀብቱ ሲበዛ ትሩፋት መጨመሩ ቀርቶ የቀደመ ሥራውንም ተወ፡፡ ለተበደለ የማይፈርድ ባለጉዳይ የሚያጉላላ ሆነ፡፡ በዚህ ጊዜ አባ ዳንኤል በሕልም እግዚአብሔር ሲቆጣውና ሲፈርድበት አየ፡፡ የማይገባ ልመና ለምኖ አውሎጊስን የቀደመ ትሩፋቱን እንዲተውና አሁን እንዲበድል ምክንያት ሆኗልና፡፡ አባ ዳንኤል በደሉ ገብቶት ከሥዕለ ማርያም ሥር ወድቆ ተማፅኖ እመቤታችን ልጇን ተማጽና ይቅር አስባለችው፡፡
                  አባ ዳንኤል በሕልም ያየው ነገር ስለከበደው ምናልባት አውሎጊስ ድሀ በድሎ ፍርድ አጓድሎ እንደሆነ ብሎ ሊያየው ቢሄድ እርሱንም የማያናግረው ሆነ፡፡ «ስለ ሰው ፍቅር የሞተ ልጅሽን ስለ አባ ዳንኤል ለምነሽ እንዳስማርሽው እኔንም ይቅር እንዲለኝ የጽጌ ልጅሽን ምሕረት ለምኝልኝ» በማለት እኛንም ባላወቅነው እየገባንና እየፈረድን ለሚመጣብን ቅጣት እንድታስምረን የሚያመለክት ነው፡፡
2.3. ኦ ረዳኢተ ድኩማን ዘይረድአኪ ኢትኃሥሢ፣
እመንበረ ላዕክኪ በምዕር ከመ ገፍታዕኪዮ ለወራሲ፣
ለገፍትዖ ፀርየ ድንግል ኃይለ ጽጌኪ ልበሲ፣
እንዘ ይሣለቅ ተአምረኪ ወሐሰተ ይሬሲ፣
መፍትውኑ ከመ ይህየው ከይሲ፡፡
                  የእመቤታችንን ተአምር አሰባስቦ የጻፈው ቅዱስ ደቅስዮስ ነው፡፡ እመቤታችንም ለዚህ ውለታው ሌላ ሰው የማይቀመጥበት ሰማያዊ ወንበር እና ሌላ ሰው የማይለብሰው አጽፍ ሰጥታዋለች፡፡ ከደቅስዮስ ዕረፍት በኋላ በእርሱ ቦታ የተሾመው ኤጲስቆጶስ በዚህ መንበር ለመቀመጥና አጽፉን ለመልበስ ሲል «ተው ይህ ለደቅስዮስ ብቻ የተሰጠ ነው» ቢሉት «እኔም እንደርሱ ኤጲስ ቆጶስ ነኝ ከእርሱ በምን አንሳለሁ)» በማለት ከወንበሩ ሲቀመጥ ወዲያው ሞቷል፡፡ ከላይ የተጻፈው ድርሰትም የሚያስረዳው ይህንን ነው፡፡ «ድኩማንን፣ ችግረኞችን የምትረጅ አንቺ ግን ረዳት የማትሽ ሆይ ከወዳጅሽ ከደቅስዮስ ወንበር ላይ በትዕቢትና በድፍረት የተቀመጠውን እንደተቀበልሽው የእኔንም ጠላቶች አጋንንትን እኩያት ኃጣውእን ለማስወገድ የጽጌሽን ማለት የልጅሽን ኃይል ይዘሽ ተነሽ» በማለት ለወዳጆቿ የምትቆም እመቤታችን ከጠላታችን እንድትታደገን ከታሪኩ አንጻር የቀረበ ጸሎት ነው፡፡
2.4. «በጌጋየ አዳም ወሔዋን ሱራፌል ዘአጸዋ፣
እንበለ ጽጌኪ መኑ ለአንቀጸ ገነት ዘአርኃዋ፣
ተፈሥሒ ድንግል መያጢተ አዳም እምጼዋ፣
በተአምርኪ ውስተ ምድረ ጽጌ አቲዋ
ከመ ጣዕዋ አንፈርዓፀት ጼዋ፡፡
                   አዳምና ሔዋን ባጠፉት ጥፋት ከገነት ተባረው ወደ ምድረ ፋይድ እንዲወርዱ ተፈርዶባቸው፡፡ ገነትን ሱራፌል መልአክ በምትገለባበጥ የእሳት ሰይፍ ይጠብቅ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ የተዘጋጀት ገነትን «እንበለ ጽጌኪ መኑ ለአንቀጸ ገነት ዘአርኃዋ፤ ያለ አንቺ ጽጌ ያለ ክርስቶስ በሱራፌል ስትጠበቅ የነበረችውን ገነት ሊከፍታት የቻለ ማንም ፍጥረት የለም» ዘፍ.3÷24፡፡ ካንቺ በተገኘ በክርስቶስ ወደ ቀደመ ክብሯና ቦታዋ የተመለሰች ሔዋን የእናቱን ጡት ጠብቶ ደስ እንደሚሰኝ እንደሚዘል እንቦሳ ደስ ተሰኘች፡፡ በአጠቃላይ ይህ የሚያስረዳው ያለ ክርስቶስ ሰው መሆንና በመስቀል ተሰቅሎ ቤዛ መሆን ማንም የገነትን በር ሊከፍት እንደማይችል ሲሆን የተዘጋውን የገነት በር የከፈተና የሰው ልጅ ያጣውን የልጅነት ጸጋ የመለሰ ክርስቶስ ደግሞ ከእመቤታችን የተገኘ መሆኑን ነው፡፡ እግዚአብሔር በኢሳይያስ አንደበት «መድኃኒቴም አይዘገይም፤ ከጽዮን ለክብር እንዲሆን መድኃኒትን ለእስራኤል ሰጥቻለሁ» ኢሳ.4÷ኮ1፡፡ እንዳለ የተዋረደው የሰው ልጅ የከበረበትና የዳነበት መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘው ጽዮንን ከተባለች ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ነው፡፡ ይህንን መድኃኒት ለዓለሙ ያበረከተች እርሷ ናት፡፡
3. ተግሣጽ
            አባ ጽጌ ድንግል ይህንን ማኅሌተ ጽጌ ሲደርስ ለመስቀልና ለእመቤታችን ክብርና ስግደት አይገባም የሚሉ ደቂቀ እስጢፋ የሚባሉ መናፍቃን ተነሥተው ነበር፡፡ በዘመኑ የነበሩት ንጉሥ አፄ ዘርዐ ያዕቆብ ጉባኤ አሠርተው አከራክረው መናፍቃኑ ተረትተዋል፡፡ አባ ጽጌ ድንግልም በማኅሌተ ጽጌ ውስጥ እነዚህን የእመቤታችንን ተአምርና ክብር በመግለጽ መናፍቃንን በመገሰጽ በዚህ የተግሣጽ ድርሰታቸው አስተምረዋል፡፡ ለምሳሌ የተወሰኑትን እንመልከት
ከመ ይትፌሣሕ ጻድቅ ሶበ ይሬኢ በቀለ፣
በተበቅሎ ፀር ያርኢ ዘተአምርኪ ኃይለ፣
እፎ የሐዩ እመአምላክ እንተ ኪያከ ፀአለ፣
አኮኑ በፍትሐ ጽጌኪ ይሙት ተብህለ፣
ላዕለ አቡሁ ወእሙ ዘአሕስመ ቃለ፡፡
            ጻድቅ እግዚአብሔር ጠላቶቹን ሲበቀልለት ሲያይ ደስ ይለዋል፡፡ ይኸውም የአንቺን ተአምር ኃይል ያሳይ ዘንድ ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ያንቺን ተአምር የሚንቁና አንቺን የማያከብሩ ከሐድያን እንዴት በሕይወት ሊኖሩ ይገባቸዋል) ምክንያቱም «በልጅሽ በክርስቶስ ትእዛዝ «እናቱን ወይም አባቱን የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል» /ዘጸ.21÷17/ ተብሎ ተፈርዷልና፡፡ እናት አባቱን የሰደበ ሞት የሚገባው ከሆነ ክርስቶስ ሰማያዊውን አምላክ ወልዳ፣ ጡቷን አጥብታ፣ አዝላ፣ ተሰዳ ለዓለም ሕይወት ባበረከተችው በድንግል ማርያም ላይ ቃልን የተናገረማ እንዴት ያለ መከራ ይጠበቀው ይሆን)
4. ምሥጢር
              በዚህ ርዕሰ ጉዳይ የምናየው በብሉይና በሐዲስ የተነገረውን እያመሰጠረ፣ በብዙ አምሳልና ትንቢት ይነገር የነበረውን የአምላክን ከድንግል መወለድ፣ ትንቢቱን ከፍጻሜው ጋር እያዛመደ የሚናገረውን ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ የተወሰኑትን እናያለን፡፡
4.1 «ዘብኪ ተባረኩ ወተቀደሱ አሕዛብ፣
 ትእምርተ ግዝረቱ ወዘርዑ ለአብርሃም አብ
ጽጌ ድንግልናኪ በግዕ ለቤዛ ይስሐቅ ውሁብ
ማርያም ፅፀ ሳቤቅ ወምሥራቅ ዘያዕቆብ
ወላዲቱ ለሥርግው/ለስግው/ ኮከብ»
              «አሕዛብ በአንቺ የተባረኩብሽ የአብርሃም የግዝረትና የዘሩ ምልክት አንቺ ነሽ፡፡ የድንግልናሽ ጽጌ በግዕ /በግ/ የይስሐቅ ቤዛ ሆኖ ተሰጠ፡፡ ማርያም ሆይ የተወደደውን ኮከብ የወለድሽ የያዕቆብ ምሥራቅ ነሽ፡፡»
                እግዚአብሔር አብርሃምን ከሀገሩና ከወገኑ ተለይቶ እርሱ ወደ ሚያሳየው ሀገር እንዲሄድ ካዘዘው በኋላ «በዘርዕከ ይትባረኩ ኩሎሙ አሕዛበ ምድር፤ በዘርህ የምድር አሕዛብ ይባረካሉ» /ዘፍ.12÷3/ ብሎ ቃል ኪዳን፣ ከአሕዛብ የሚለይበትና እግዚአብሔርን የሚያመልክ መሆኑ የሚታወቅበት ምልክት የሚሆን ግዝረትን ሰጠው፡፡ እንዲህ ሲል «በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳን ይህ ነው፡፡ ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ፡፡ በእኔና በአንተ ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል» /ዘፍ.17÷9-11/፡፡ «አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉ» የሚለው ተስፋ በይስሐቅ አልተፈጸመም፡፡ ምክንያቱም በሰው ላይ የተጣለው ርግማን በይስሐቅ አልተወገደም በይስሐቅ የሚወገድ ቢሆን ኖሮ ይስሐቅ በተሰዋና ዓለምን ባዳነ ነበር፤ ክርስቶስም ወደዚህ ዓለም መምጣትና መሞት ባላስፈለገው ነበር፡፡ ስለዚህ ያ በዘርህ አህዛብ ይባረካሉ ተብሎ ለአብርሃም የተነገረው ተስፋ የተፈጸመው ክርስቶስ ከእመቤታችን በድንግልና ሲወለድ ሰው ሲሆን ነው፡፡ አምላክ ሊዋሐደው የሚችል ንጹሕ ሥጋና ነፍስ ይዛ ተገኝታ ለአብርሃም የተነገረውን ተስፋ እንድናገኝ አድርጋለችና፡፡
                  ለአብርሃም የተሰጠው ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ያንጊዜ ያመነና ያላመነ የሚለው በግዝረት እንደነበረ ሁሉ ዛሬ ደግሞ በሕዝብና በአሕዛብ መካከል መለያው ምልክቱ ጥምቀት ነው፡፡ ከአሕዛብ የሚለየንን፣ የእግዚአብሔር ልጆችና የመንግሥቱ ወራሾች የሚያደርገንን ጥምቀት ተጠምቆ ተጠመቁ ያለንን ክርስቶስን ያገኘነው ከእመቤታችን በመወለዱ ነው፡፡ ለዚህ ነው
«ዘብኪ ተባረኩ ወተቀደሱ አሕዛብ
ትእምርተ ግዝረቱ ወዘርዓ ለአብርሃም አብ»
ያለው፡፡ ክርስቶስ ሰው የሆነው ከአብርሃም ዘር ነው፡፡ /ዕብጠ2.16/፡፡ ክርስቶስን ያስገኘች እመቤታችን የአብርሃም ዘር መሆኗን ወንጌላዊው ማቴዎስ በምዕራፍ አንድ በሚገባ አስረድቷል፡፡ ለአብርሃም የተሰጠው ተስፋ በእርሱ አማናዊ መሆኑንም ያጠይቃል፡፡
4.2 ጽጌ ድንግልናኪ በግዕ ለቤዛ ይስሐቅ ወሁብ
ማርያም ፅፀ ሳቤቅ ወምስራቅ ዘያዕቆብ
ወላዲቱ ለሥርግው ኮከብ
ይስሐቅ ለመሥዋዕት በቀረበ ጊዜ ከመሞት ያዳነው በግ ከዚህ መጣ ሳይባል በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ ተገኝቷል፡፡ /ዘፍጠ22.13/፡፡ አብርሃም በጉን ሰውቶ የታሰረውን ይስሐቅን ፈትቶታል፡፡ ይስሐቅ የዓለሙ ምሳሌ ሲሆን በጉ የክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ በጉ የተያዘበት ዕፀ ሳቤቅ ደግሞ የእመቤታችን ምሳሌ ነው፡፡ በጉ በዕፀ ሳቤቅ ታስሮ እንደተገኘ ክርስቶስ ሰው የሆነው ከእመቤታችን ነው፡፡ ያ በግ ቤዛ ሆኖ ይስሐቅን ከሞት እንዳዳነው ሁሉ ክርስቶስም ስለ ዓለሙ ኃጢአት ሞቶ ለዓለሙ ቤዛ ሆኖአል፡፡ /ዮሐጠ3.16ጠ17/፡፡
ደራሲው የምሳሌውን መፈጸም ካስረዳ በኋላ «ወምሥራቅ ዘያዕቆብ» ይላል፡፡ በለዓም « ኮከብ ይሠርቅ እም ያዕቆብ ወየአትት ኃጢአተ እም እስራኤል፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል ኃጢአተኝነትንም ከእስራኤል ያስወግዳል. . .» ብሎ ትንቢት የተናገረለትን ኮከብ የወለደች እርሷ መሆኗን የሚያስረዳ ነው፡፡ /ዘኁል.22.17 ፤ኢሳ.27.9፣59.20፤ ሮሜ.11.26/ ፡፡
4.3. «ሰመዩኪ ነቢያት እለርእዩ ኅቡአተ፣
ገነተ ጽጌ ዕፁተ ወኆኅተ ምሥራቅ ኅትምተ፣
እግዚአብሔር ወሀበ እንዘ ይብል ለቤተ ዳዊት ትእምርተ
ከመ ትፀንሲ ድንግል ወትወልዲ ሕይወተ
ኢሳይያስኒ ነገረ ክሡተ፡፡»
ትርጉም
           «ምሥጢርን ያዩ ነቢያት የተዘጋች የምሥራቅ በር የታተመች ገነት እያሉ ጠሩሽ፡፡ እግዚአብሔር ለዳዊት ቤት ድንግል በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ በኢሳይያስ አማካኝነት በግልጽ ተናገረ፡፡»
         ከሩቅ ያለውንና ወደፊት የሚሆነውን በትንቢት መነጽር አቅርበው ያዩና ሥውሩ ምሥጢር የተገለጠላቸው ነቢያት «ገነተ ጽጌ ዕፁተ፤ ወልኅተ ምሥራቅ ኅትምተ፤ የታተመች ምንጭ የተዘጋች የምሥራቅ በር» እያሉ ጠሩሽ፡፡
          ሰሎሞን በመኃልዩ ፡ «እኅቴ ሙሸራ የተቆለፈች ገነት የተዘጋ ምንጭ ናት» ይላታል፡፡ በዚህም እመቤታችንን
ሀ/ በተቆለፈች ገነት
ለ/ በታተመች ምንጭ መስሏታል፡፡ ለምን?
ሀ/ የተቆለፈች ገነት
           በውስጥዋ አትክልት ሲኖር ነገር ግን ወደዚህች ቦታ የሚደርስ የለም ተቆልፎአልና፡፡ እመቤታችንም በንጽሕናና በድንግልና የታጠረች ስለሆነች ከእርስዋ የተወለደ አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡
           የተክል ቦታ ዘር ሳይዘራባት ወይንም ተክል ሳይተከልባት እንዲሁም የሚንከባከበው ሳይኖር ሊያፈራ አይችልም፡፡ ይህች ገነት ምንም ነገር የማይደርስባት የተቆለፈች ስትሆን አትክልት ግን አለባት፡፡ እመቤታችንም በድንግልናና በንጽሕና የፀናች ስትሆን እንበለ ዘር ክርስቶስን አስገኝታለች፡፡
ለ/ የታተመች ምንጭ
            ምንጩ የታተመ ሲሆን ነገር ግን ውኃ ያለው ነው፡፡ እመቤታችንም በድንግልና የፀናች ስትሆን በእናትነት ክርስቶስን ወልዳለች፡፡ ሕዝቅኤልም «ወርኢኩ ኆኅተ በምሥራቅ፣ ኅቱም በዐቢይ መንክር ማኅተም አልቦ ዘቦኦ ዘእንበለ እግዚእ ኃያላን ቦአ ውስቴታ ወወጽኣ. . .፤ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተው በስተውጭ ወዳለው ወደ መቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም ሰውም አይገባበትም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል፡፡» አለኝ ይላል፡፡ /ሕዝቅ.44÷1- 3/፡፡
            የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ማለቱ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ ፍፁም ሰው ሆኖ ከእርስዋ ተፀንሶ ተወልዷልና ነው፡፡
             ይህ ሕዝቅኤል ያየው ሕንፃ በጥሬ ትርጉሙ ተወስዶ ቤተመቅደስ ነው እንዳይባል ቤተመቅደስ የሚሠራው ሕዝቡ አምልኮቱን ሊፈጽምበት ስለሆነ ከተሠራ በኋላ ለምን ይዘጋል) «በመካከላቸው አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ)» እንዲል፡፡/ዘጸ.25÷8፡፡/
            ይኸው ነቢይ ስለ ቤተመቅደስ በተናገረበት ቦታ «. . . ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን ፡፡ የደኅንነቱን መሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ ወደ ምሥራቅ የሚመለከተው በር ይከፈትለት» ይላል፡፡ /ምዕ.46÷12/፡፡ ሰሎሞንና ሕዝቅኤል ስለእርስዋ የተምሳሌትነትና በትንቢት የተናገሩላት እርስዋ ድንግል ማርያም መሆንዋን ከዘከረ በኋላ ነቢያት ብቻ ሳይሆኑ ራሱ እግዚአብሔርም ምልክት መስጠቱን እንዲህ ሲል ይገልጻል፡፡ «እግዚአብሔር ወሀበ እንዘ ይብል ለቤተ ዳዊት ትእምርተ ከመ ትፀንሲ ድንግል ወትወልዲ ሕይወተ ኢሳይያስኒ ነገረ ክሡተ» ይላል፡