ቅዳሜ 11 ኤፕሪል 2015

አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ(2ቆሮ 5-14)


ከጌታችንና ከአምላካችን ከመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊት መሰቀል የወንበዴ መቅጫ መሳሪያ ነበር። ሰውን በመስቀል ላይ መቅጣት የተጀመረው በፋርስ ነው። ፋርስ የዛሬዋ ኢራን ናት።የፋርስ ሰዎች “ኦርሙዝድ” የተባለ “የመሬት አምላክ” ያመልኩ ነበር። ከዚህም የተነሳ ”ወንጀለኛው ቅጣቱን በመሬት ላይ የተቀበለ እንደሆነ አምላካችን ይረክሳል” ብለው ስለሚያምኑ ወንጀለኛውን ከመሬት ከፍ አድርገው በመስቀል ላይ ይቀጡት ነበር። ይህም ቅጣት ቀስ በቀስ በሮም ግዛት ሁሉ የተለመደ ህግ ሆነ። ከዚህም ሌላ በኦሪቱ ስርዓት  ቅጣታቸውን በመስቀል ላይ የሚሰቀሉ ሰዎች ርጉማንና ውጉዛን ነበሩ። ይህንንም እግዚአብሄር ለሙሴ “ማንም ሰው ለሞት የሚያበቃውን ሃጥአት ቢሰራ፤ እንዲሞትም ቢፈረድበት፤ በእንጨትም ላይ ብትሰቀለው በእንጨትም ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና ሬሳው በእንጨት ላይ አይደር” ሲል ነግሮታል(ዘዳ.21፦22)።
ትምህርት
“በመስቀል ላይ ተሰቅሎ የሚሞት የተረገመ ከሆነ ለምን ጌታችን በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ?”
  • ·         ቅጣታችንን ተቀብሎ ሞተ፦የሁላችንንም በደል በራሱ ላይ አኖረ።(ኢሳ.53፦6)
  • ·         የእኛን ሞት ሞተ፦በአንድ ሰው ምክንያት ሞት ወደዓለም ገባ ተብሎ አንደተጻፈው (ሮሜ.5፦15)
  • ·         ፈውስ እናገኝ ዘንድ ሞተ፦በእርሱ ቁስል አኛ ተፈወስን።(ኢሳ53፦5)
  • ·         ገነትን አንወርስ ዘንድ መርገማችንን ወስዶ ሞተ፦በእንጨት የተሰቀለ የተረገመ ነው። ተብሎ እንደተጻፈው(ዘዳ.21፦23)
  • ·         ሙታንን ያነሳ ዘንድ ሞተ
  • ·         የዳያብሎስን ምክር ያፈርስ ዘንድ ሞተ


አንዱ ስለ ሁላችን ሞቶ ምን አገኘን?
1.  ሕወትን አግኝተናል፤
በኃጥያት ምክንያት ሞት ገዝቶን ሞት ነግሶብን እነኖር ነበር። ኃጢአት በዘር የእተላለፈም ሁላችንም በአዳም ኃጢአት ምክንያት እንሞት ነበር።በመሆኑም ሞት ከአዳም እስከ ሙሴ ድረስ በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ነግሶ ነበር(ሮሜ5፦12)። ከክርስቶስ ሞት በኋላ ግን በክርስቶስ ሞት ስለተሻረ አጥተነው የነበረውን ሕይወት አግኝተናል።”ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና” (1ኛቆሮ፣15፦22)። በተጨማሪም “እኛ ሁላችን ደግሞ በስጋ ምኞት እንኖር ነበር፤ አንደሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን።  ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጠጋ ስለሆነ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሳ በበደላችን ሞታን እንኳ በሆንን ጊዜ ሕይወትን ሰጠን (ኤፌ.2፦3-5)።
ኃጢአት ወደ ዓልም ገብቶ ሞት የመጣብን በመብል ምክንያት ነው።(ዘፍ.3፦1-24)
2.  ሰላምን አግኝተና፤
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፦”ሰላምን እተውላችኋለሁ ሰላሜን አሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም፤” ብሎ እንደተናገረ ፍጹም የሆነውን ሰላም የሰጠን በመስቀል ላይ ነው።
3.  አዲስ ሰው ሆነናል፤
በኃጢያት አርጅቶ የነበረው ሰውነታችን አዲስ የሆነው በመስቀል ላይ በተፈጸመው ቤዛነት ነው። “ከአንግዲህስ ወዲያ በኃጢአት አንዳንገዛ የኃጢአት ስጋ ይሻር ዘንድ አሮጌው ሰውነታችን ከእርሱ ጋር አንደተሰቀለ እናውቃለን።(ሮሜ.6፦6)
4.  ከራሱ ጋር አስታረቆናል፤
በኃጢያት ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ተጣልተን አንኖር ነበር።ይሁን አንጂ አኛ በበደልን አርሱ ክሶ በቤዛነቱ መልሶ ታርቆናል።”ጠላቶቹ ሳለን ከእግዚያብሔር ጋር በልጁ ሞት ከተታረቅን፦ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ አንድናለን፤ ይህም ብቻ አይደለም፦ነገር ግን አሁን መታረቁን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግም አንመካለን፤”(ሮሜ.5፦10)።
መልእክት
አንዱ ስለ ሁላችን ሞተ፣ የእኛን ቅጣት ወሰደ፣ እኛ በእርሱ ሞት ወደ ቀደመ ክብራችን እንመለስ ዘንድ ሞተ ።መርገማችንንም ወሰደ።የኢየሱስ ክርስቶስን ስቅለት ስናስብ የተጣላን መታረቅ አለብን። የኢየሱስ ክርስተቶስ ሞት የሰው ልጆች የጥል ግድግዳ ፈርሶ ፍቅር የተመሰረተበት ዕለት ነውና።ይህን ውለታ አንዳንረሳ።

እሑድ 5 ኤፕሪል 2015

***ተሰጥዖ***

***ተሰጥዖ***
በሰሞነ ሕማማት ከሰኞ - ዓርብ እየሰገድን ተሰጥዖ የምንቀበላቸው ( በቃል የምንላቸው ) ከአሁን ጀምረን እንድንለማመዳቸው እንሆ ብለናል፡፡
• ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወዕዘዝ እስከ ለዓለም (ለአንተ ኃይልክብር ጌትነት ገዥነት ለዘለዓለሙ ገንዘብህ ነው
• አማኑኤል አምላኪየ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወዕዘዝ እስከ ዓለም (ፈጣሬዬ አማኑኤል ሆይ ኃይል ክብር ጌትነት ገዥነት ለዘለዓለሙ የአንተ ነው)
• ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወዕዘዝ እስከ ለዓለም (ጌታዬ ኢየሱስ ድርስቶስ ሆይ ኃይል ክብር ጌትነት ገዥነት ለአንተ ይገባል)
• ኃይልየ ወፀወንየ ዉእቱ እግዚእየ እስመ ኮንከኒ ረዳእየ እብል በአኮቴት አቡነ ዘበሰማያት እስከ ይእቲ መንግሥት ኃይል ወስግሐት ለዓለም ዓለም ድረስ ብቻ
• ኃይሌና አምባዬ መጠጊያዬ እርሱ ጌታዬ ነው ረዳቴ ሆነህልኛልና በምስጋና እንዲህ እላላው አባታችን ሆይ እስከ ኃይል ክብር ምሥጋና ለዘለዓለሙ አሜን ድረስ ብቻ
ካህናት፡- ጸልዩ በእንተ ጽንዐ ዛቲ መካን ወኲሎን መካናት እንተ አበዊነ ቅዱሳን ወገዳማት አዕሩግ እለ የኅድሩ ውስቴቶን ወዕቀበተ ዝንቱ ዓለም በምልዑ ከመ ይዕቀቦሙ እግዚእ ምኲሉ እኲይ ወይሥረይለነ ኃጣውኢነ፡፡
ሕዝብ፡- እግዚኦ ተስሃለነ
ካህናት፡- ስለዚች ቦታ መጽናት በቅዱሳን አባቶች ስም ስለሚጠሩም ቦታዎችና ገዳማት በውስጣቸውም ስለሚኖሩ ሽማግሎች በጠቅላላው ስለዚህ ዓለም መጠበቅ ጌታ ከክፋ ሁሉ ይጠብቃቸው ዘንድ የእኛንም ኃጢአት ያስተሰርይ ዘንድ ጸልዩ
ሕዝቡ፡-አቤቱ ይቅር በለን
ከላይ ያለውን ዓይነት ጸሎት በግእዝ ወይም በአማርኛ በሚጸለይበት ጊዜ በመሐል በመሐል እግዚኦ ተስሃለነ ወይም አቤቱ ይቅር በለን እያለን እሰግዳለን 22 ጊዜ ይባላል፡፡
ኪርያላይሶን ኪርያላይሶን ኪርያላይሶን
ኪርያላይሶን አብናዲ ናይናን ኪርያላይሶን
ኪርያላይሶን ታኦስ ናይናን ኪርያላይሶን
ኪርያላይሶን ማስያስ ናይናን ኪርያላይሶን
ኪርያላይሶን ኢየሱስ ናይናን ኪርያላይሶን
ኪርያላይሶን ክርስቶስ ናይናን ኪርያላይሶን
ኪርያላይሶን አማኑኤል ናይናን ኪርያላይሶን
ኪርያላይሶን ትስቡጣ ናይናን ኪርያላይሶን
ከዚህ በኋላ ኪርያላይሶን ብቻ በመቀባበል በተናጥል 20 ጊዜ ይባላል፡፡

***በዕለተ ዓርብ ከጠዋት ሦስት ሰዓት ጀምሮ እስከ 12 ሰዓት የምንቀበላቸው***
• ጠዋት ሦስት ሰዓት
ዲያቆን፡- ከመዝሙረ ዳዊት ላይ መዝ 21፡17 በዜማ ይላል ‹‹እግዚኦ ኢትጸመመኒ ለክስትየ እስመ
አፈ ዐማፂ ወአፈ ኃጥእ አብቀው ላዕሌየ ወነበቡ ላዕሌየ በልሳነ ዐመፃ››
ትርጉም፡- አቤቱ ልመናዬን ቸል አትበል የኃጢአተኛና የተንኮለኛ አፍ በላዬ ላይ
ተነቃንቀውብኛልና የሽንገላን አንደበትም በላዬ ላይ ተናገሩ፡፡
ካህኑ፡- የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 27 ከቁትር 15 እስከ 26 ካነበቡ በኋላ
በሕብረት ፡- ‹‹ጊዜ ሠለስቱ ሰዓት አኃዝዎ ለኢየሱስ ወወስድዎ ይሰቅልዎ›› እየተባለ ይሰገዳል
ትረጉም፡-ሦስት ሰዓት በሆነ ጊዜ ኢየሱስ ይዘው ይሰቅሉት ዘንድ ወሰዱት
ካህኑ፡- የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 15ከቁጥር 6እስከ 15 ካነበቡ በኋላ
በሕብረት፡- ‹‹ጊዜ ሠለስቱ ሰዓት አሕየወ ሎሙ በርባንሀ ወወሀቦሙ ኢየሱስሀ ይስቅሉ›› እየተባለ ይሰገዳል
ትርጉም፡-ሦስት ሰዓት በሆነ ጊዜ በርባንን አድኖ ኢየሱስን ይሰቅሉት ዘንድ ሰጣቸው
ካህን፡- የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 23 ከቁጥር 13 እስከ 25 ካነበቡ በኋላ
በሕብረት፡- ‹‹ጊዜ ሠለስቱ ሰዓት ወሰድዎ ለኢየሱስ ውስተ ዐውደ ምኲናን›› እየተባለ ይሰገዳል
ትርጉም፡- ሦስት ሰዓት በሆነ ጊዜ ጌታ ኢየሱስን ወደ ፍርድ አደባባይ ወሰዱት
ካህን የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 19፡1-12 ካነበቡ በኋላ
በሕብረት፡- ‹‹ጊዜ ሰለስቱ ሰዓት ቀስፎ ጲላጦስ ለኢየሱስ ወመጠዋሙ ይስቅልዎ ››
ትረጉም፡- ሦስት ሰዓት በሆነ ጊዜ ጌታ ኢየሱስን ገርፎ ይሰቅሉት ዘንድ ሰጣቸው
• በስድስት ሰዓት
ዲያቆን፡- ከወንጌል አስቀድሞ መዝ 21፡16-17
‹‹ቀመዉኒ እደውየ ወእገርየ ወኈለቁ ኲሉ አዕፅምትየ እሙንቱሰ ጠይቆሙ ወተዐወሩኒ›››
ትርጉም፡- እጄንና እግሬን ቸነከሩኝ አጥንቶቼንም ሁሉቆጠሩ እነሱስ አውቀው ተረድተው ቸል አሉኝ
ካህኑ፡- የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 27 ከቁጥር 27 እስከ 45 ካነበቡ በኋላ
በሕብረት፡- ‹‹ጊዜ ስዲስቱ ሰዓት አልበስዎ አልባሲሁ ለኢየሱስ ወወሰድዎ ይስቅልዋ››
ትርጉም፡- ስድስት ሰዓት በሆነ ጊዜ ኢየሱስን ልብሱን አልብሰው ይሰቅሉት ዘንድ ወሰዱት
ካህን፡- የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 15 ቁትር 16 እስከ 33 ካነበቡ በኋላ
በሕብረት፡- ‹‹ጊዜ ስድሰቱ ሰዓት ቀትር ሶቤሃ ሊቃነ ካህናት ሰቀልዎ ለኢየሱስ በቀራንዮ መካን››
ትርጉም፡- ስድስት ሰዓት በሆነ ጊዜ ያን ጊዜ ቀትር ነበር የካህናት አለቆች ኢየሱስን ቀራንዮ ሰቀሉት
ካህን፡- የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 23 ቁጥር 27 እስከ 44 ካነቡቡ በኋላ
በሕብረት፡- ‹‹ጊዜ ስድስቱ ሰዓት አበጥዎ ለስምዖን ከመ ይጹር መስቀሎ›› እየተባለ ይሰገዳል
ትረጉም፡-ስድስት ሰዓት በሆነ ጊዜ መስቀሉን ይሸከም ዘንድ ስምዖንን አስገደዱት
ካህን፡- የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 19 ቁጥር 13 እስለ 27 ካነቡቡ በኋላ
በሕብረት፡- ‹‹ጊዜ ስድስቱ ሰዓት ሰቀልዎ ለኢየሱስ ማእከለ ክልኤ ፈያት›› እየተባለ ይሰገዳል
ትርጉም፡- ስድስት ሰዓት በሆነ ጊዜ የካህናት አለቆች ጌታ ኢየሱስን በሁለት
• በዘጠኝ ሰዓት
ዲያቆን፡- ከወንጌል በፊት መዝ 68፡21-12 በዜማ ይላል ‹‹ወወደዩ ሐሞተ ውስተ መብልዕየ ወአስተዩኒ ብሒአ ለጽምትየ ወለትኩኖሙ ማእዶሙ መሥገርተ በቅድሜሆሙ››
ትርጉም፡- በምግቡ ውስጥ ሐሞት ጨመሩ ጥማቴንም ለማርካት መፃፃን አጠጡኝ ማዕዳቸው
በፊታቸው ወጥመድ ትሁንባቸው
ካህን፡-የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 27፡46-50 ካነበቡ በኋላ
በሕብረት፡-‹‹ጊዜ ተሠዓቱ ሰዓት ጸርሐ ኢየሰሱስ በቃሉ ወይቤ ኤሎሄ ኤሎሄ›› እተየባለ ይሰገዳል
ትርጉም፡- ዘጠኝ ሰዓት በሆነ ጊዜ ኢየሱስ ቃሉን አሰምቶ ኤሎሄ ኤሎሄ አለ
ካህን ፡- የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 15፡34-35 ካነበቡ በኋላ
በሕብረት፡- ‹‹ጊዜ ተሰዓቱ ሰዓት ከልሐ ኢየሱስ በቃሉ ወአማኅፀነ ነፍሶ ሶቤሃ›› እየተባለ ይሰገዳል
ትርጉም፡- በዘጠኝ ሰዓት ጌታ ኢየሱስ ቃሉን አሰምቶ ተናገረ ያንጊዜም ነፍሱን አደራ ሰጠ
ካህን፡- የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 23፡45-46 ካነበቡ በኋላ
በሕብረት፡- ‹‹ጊዜ ተሰዓቱ ሰዓት ገዓረ ኢየሱስ በቃሉ ወወጽአት መንፈሱ ሶቤሃ›› እየተባለ ይሰገዳል
ትርጉም፡- በዘጠኝ ሰዓት ጌታ ኢየሱስ ቃሉን አሰምቶ ጮኸ ያን ጊዜ ነፍሱ ከሥጋው ተለየች
ካህን፡- የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ19፡28-30 ካነበቡ በኋላ
በሕብረት፡- ‹‹ጊዜ ተሰዓቱ ሰዓት አጽናነ ርእሶ ኢየሱ ወይቤ ተፈጸመ ኲሉ›› እየተባለ ይሰገዳል
ትርጉም፡- በዘጠኝ ሰዓት ጌታ ኢየሱስ ራሱን ዘንበል (ዘለስ) አድርጎ ሁሉ ተፈጸመ አለ
-----------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
• አስራ አንድ ሰዓት
ዲያቆን፡- ከወንጌል በፊት አስቀድሞ መዝ 142፡6 በዜማ ይላል ‹‹አንሣእኩ እደውየ ኀቤከ ነፍስ የኒ ከመ ምድረ በድው ጸምዐተከ ፍጡነ ስምዐኒ እግዚኦ ኀለፈት ነፍስየ››
ትርጉም፡- እጆቼን ወደ አንተ አነሳው ሰውነቴንም በምድረ በዳ ዝናምን እደናፈቀ አንተን ናፈቀች አቤቱ ሰውነቴን
እለይ እለይ ብላላችና ፈጥነህ ስማን
ካህን፡- የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 27፡51፡56
ካህን፡- የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 15፡38-41
ካህን፡- የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 23፡47-49
ካህን፡- የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 19፡31-37

ቅዳሜ 4 ኤፕሪል 2015

...ሆሣዕና..

...ሆሣዕና...
መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ (PhD Candidate)
የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲሳት ትርጓሜ መምህር
ሆሣዕና ማለት የዕብራይስጥ ቃል ሲኾን “ሆሻአና” ሲባል ትርጒሙም “አቤቱ አኹን አድን” ማለት ነው፤ ይኽ በዓለ ሆሣዕና ከ9ኙ ዐበይት የጌታ በዓላት ውስጥ ሲኾን ኪሩቤል ሱራፌል በፍርሀት በረዐድ ኹነው ዘፋኑን የሚሸሙት ጌታ በትሕትና በአህያና በውርንጫይቱ በትሕትና ተቀምጦ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት፣ የዘካርያስ ትንቢት የተፈጸመበት፣ ሕዝቡ ዘንባባ ይዘው የዘመሩበት፣ ሕጻናት በንጹሕ አንደበታቸው ሆሣዕና ብለው ያመሰገኑበት ታላቅ በዓል ነው፡፡
ይኽም ታሪክ በ4ቱ ወንጌላት ላይ ሲጻፍ በማቴ 21፡1 ላይ “ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ” ይላል ቤተ ፋጌ ማለት የበለስ ቤት ማለት ሲኾን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ በሚወስደው መንገድ አቅራቢያ ያለች ትንሽ መንደር ስትኾን ኹሉን ዐዋቂ የኾነው ጌታ ጴጥሮስንና ዮሐንስን “በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ” ብሏቸዋል፡፡
“ማንም አንዳች ቢላችሁ ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል” በማለት የኹሉ ፈጣሪ የኹሉ ጌታ መኾኑን አመለከታቸው፤ በተሰጣቸው ሥልጣነ ክህነት የሕዝቡንም የአሕዛቡን ኀጢአት የማሰር የመፍታት ሰማያዊ ሥልጣነ ክህነት የተሰጣቸው ሐዋርያትን የሕዝብ ምሳሌ የኾነችውን አህያይቱንና የአሕዛብ ምሳሌ የኾነችው ውርንጫዋንም አመጡለት፥ ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ”
በአህያዋና በውርንጫዋ ላይ ኮርቻ ሳይኾን ልብስ ማድረጋቸው ኮርቻ ይቈረቊራል ልብስ ግን አይቈረቊርምና የማትቈረቊር ሕግ ሠራኽልን ሲሉ፤ ዳግመኛም ልብስ በአካል ያለውን ኀፍረት እንዲሰውር አንተም በደላችንን የምትሰውርልን ይቅር ባይ ነኽ ሲሉ፡፡
ከኢየሩሳሌም እስከ ቤተ መቅደስ 16 ምዕራፍ ሲኾን መተርጒማን እንደሚገልጹት 14ቱን ጌታ በእግሩ ሲኼድ 2ቱን በአህያዋ፤ በውርንጫዋ 3 ጊዜ ቤተ መቅደሷን ዞሯል፡- 14ቱ በእግሩ መኼዱ የ10ሩ ቃላት 4ቱ የ4ቱ ኪዳናት ምሳሌ፡፡ 2ቱ በአህያዋ መጓዙ የፍቅረ እግዚአብሔርና የፍቅረ ቢጽ፤ 3ቱን በውርንጫዋ ተቀምጦ ቤተ መቅደሱን መዞሩ የ3ትነቱ የአንድነቱ ምሳሌ ነበር፡፡
ክብር ይግባውና ጌታ ንጉሠ ነገሥት ሲኾን፤ ኪሩቤል ሱራፌል ዙፋኑን በፍርሀት በረአድ የሚሸከሙት 24ቱ ካህናተ ሰማይ ዙፋኑን በፍርሀት የሚያጥኑለት ርሱ በትሕትና የዋህ ኾኖ በተናቁት በአህያና በውርንጫይቱ ላይ ተቀመጠ፤ ይኽም የተናቁትን ሊያከብር እንደመጣና፤ በየዋሀን ምእመናን ልቡና እንደሚያድር ለማሳወቅ በነርሱ ተቀመጠ፤ በአህያ የተቀመጠ አባሮ እንደማይዝ ሸሽቶ እንደማያመልጥ ርሱም ካልፈለጉት እንደማይገኝ ከፈለጉት እንደማይታጣ በምስጢር አመለከታቸው፡፡
ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ፡- ስለዚኽ ነገር በትርጓሜ ወንጌሉ ላይ “እነዚኽ እንስሳት መላውን የሰው ልጅ ይወክላሉ፡፡ ኹለቱም አህያ መኾናቸውም የሰው ልጅ ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የነበረውን አኳኋን የሚያስረዳ ነው፡፡ ምክንያቱም አህያ በኦሪቱ ዘንድ ንጹሕ እንስሳ አይደለችም፤ ብዙ ክብደት ያላት የማትወደድ እንስሳ ናት፤ ዲዳ ናት፤ ደካማ ናት፡፡ ሰውም እንደተናገርን ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት እንዲኽ ነበረ፡፡” በማለት ሲያመሰጥር ሊቁ ቅ. ቄርሎስ ዘእስክንድርያም፡- “ፈጣሬ ኵሉ እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ጠቢብ አድርጐ ፈጥሮት ነበር፡፡ ማሰብና ማሰላሰል የሚችል ፍጥረት አድርጐ ፈጥሮት ነበር፡፡ ሰይጣን ግን አታለለው፡፡ ምንም እንኳን ሰው በሥላሴ አምሳል ቢፈጠርም መልኩን አበላሸው፡፡ ፈጣሬ ኵሉ እግዚአብሔርን ማወቅ ተሳነው፡፡ ክፉው ሰይጣን ሰውን እንስሳ እስኪመስል ድረስ ክብሩን አዋረደው፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት፡- “ሰውስ ክብሩን አላወቀም፤ የሚጠፉ እስሳትን መሰለ” ያለውም ስለዚኹ ነው /መዝ.49፡12/፡፡ በመኾኑም አህያይቱ ክብራቸውን አጥተው ተዋርደው የነበሩትን እስራኤል ዘሥጋን ትመስላለች፡፡ እስራኤል ከሕጉ ጥቂት ነገርን ያውቃሉ፡፡ ከነቢያትና ከቅዱሳንም ትንሽ ያውቃሉ፡፡ ከኹሉም በላይ ደግሞ ወደ አሚን የሚጠራቸውን ክርስቶስን አልታዘዙትም፡፡ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ሲላቸውም እንደምን እንደ አሕያይቱ በድንቁርና ተይዘው እንደነበረ ሲገልጥላቸው ነው፡፡ ውርንጫይቱ ደግሞ አሕዛብን ትወክላለች፡፡ ውርንጫ እኽልን ለመጫን እንደማታገለግል ኹሉ አሕዛብም ማኅደረ እግዚአብሔር ከመኾን ርቀው ነበርና፡፡” በማለት ገልጽዋል፡፡
ሊቁ ጀሮምም፡- “ደቀ መዛሙርቱ አህያይቱንና ውርንጫይቱን ለመፍታት ኹለት ኾነው መላካቸው ለሕዝብም ለአሕዛብም መላካቸው ያመለክታል፡፡” • አምብሮሲስ፡- “አህያየቱን ለመፍታት ማንም አይከለክላችኁም ብሎ መላኩ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ሥልጣን ሰማያዊ መኾኑ ያመለክታል፡፡” በማለት ልዩ ምስጢርን አስተላፎበታል፡፡
ያን ጊዜ ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ ይኽንም ማድረጋቸው ስንኳን አንተ የተቀመጥኽባት አህያ መሬት መርገጥ አይገባኽም ሲሉ ነበር፤ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር
ይኽም ዘንባባ ብዙ ምሳሌ ያለው ነው፤ ይኸውም በእስራኤል ያለው ሰሌን፣ ተምር፣ ዘይት ነበርና ያነን ቈርጠው አመስግነውታል፤ ይኽም ምሳሌነት ያለው ነው፤ ይኽም ሰሌን እሾኻማ እንደኾነ ትእምርተ ኀይል ትእምርተ መዊእ አለኽ ሲሉ ነው፤ እሳት ለብልቦ ይተወዋል እንጂ እንደማያቃጥለው ባሕርይኽ አይመረመርም ሲሉ ነበር፡፡
ዳግመኛም ከሰሌን ዝንጣፊ ጋር ተመሳሳይ ተምር ይዘዋል ይኽም ተምር ልዑል ነው አንተም ልዑለ ባሕርይ ነኽ ሲሉ፤ ፍሬው አንድ እንደኾነ አንተም ዋሕደ ባሕርይ ነኽ ሲሉ፡፡ በእሾኽ የተከበበ ነው ባሕርይኽ አይመረመርም ሲሉ ነበር፡፡
የዘይት ዛፍ ነው ቢሉ ዘይት ጽኑዕ እንደኾነ ጽኑዐ ባሕርይ ነኽ ሲሉ፤ ብሩህ ነው ብሩሀ ባሕርይ ነኽ በትምህርትኽም የሰውን ልቡናን ታበራለኽ ሲሉ፤ ዘይት መሥዋዕት እንደሚኾን መሥዋዕት ትኾናለኽ ሲሉ ነበር፡፡
“የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር” በማለት በአርያም መድኀኒት እንደኾነና እግዚአብሔር አብ “የምወድደው ልጄ ይኽ ነው” ብሎ መስክሮለት የመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስን የሚያርቅ በረከተ ሥጋን በረከተ ነፍስን የሚያድል መኾኑን ኹሉም መሰከሩለት፡፡
በእጅጉ የሚደንቀው የ40 ቀን የ80 ቀን ሕጻናት የፈጠራቸው ጌታ በአህያና በውርንጫ ተቀምጦ ባዩት ጊዜ በንጹሕ አንደበታቸው አንደታቸው ረቶላቸው ጌታን ዘንባባ በመያዝ ሲያመሰግኑ በእጅጉ ይደንቅ ነበር፤ ነገር ግን ጸሐፍት ፈሪሳውያን ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት፤ ኢየሱስም፦ እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? በማለት በሕጻናት እንደሚመሰገን የነርሱም ጌታ መኾኑን ከዳዊት መዝሙር በመጥቀስ ነገራቸው፡፡

ሊቁ ያዕቆብ ዘሥሩግ ሰለዚኽ ምስጢር ሲገልጸው ፡- “ፍቅርኅ ከዘባነ ኪሩብ አውርዶ በአህያ ዠርባ ላይ እንድትቀመጥ አስገደደኅ፡፡ ብዙ ዓይንና ብዙ ገጽ ካላቸው ከሠራዊተ መላክእት ይልቅ በዲዳዋ አህያ ትመሰገን ዘንድ ወደደክ፡፡ በሰማይ ሠራዊት ሠረገላ ተቀምጠኅ ክብርኅን ማሳየት አልወደድክም፤ በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጠኅ ወደ ሰማይ ሠራዊት መኼድን መረጥክ እንጂ፡፡ በአርያም እሳታውያን የሚኾኑ ኪሩቤል ያመሰግኑኻል፤ በምድርም ሕፃናት ይዘምሩልኻል፡፡ በአርያም ብርሃናውያን መላእክት በብርሃን ክንፋቸው መንገድኽን ያነጥፉልኻል፤ በምድርም ደቀ መዛሙትኽ ልብሳቸውን አንጥፈው መንገድኽን አስተካከሉ፡፡ ወዮ! አርያማዊ ሲኾን ምንም ሳይንቀን ይጐበኘን ዘንድ ከአባቱ መጣ፡፡ እርሱም በገዛ ፈቃዱ ሰው እስከ መኾን ደርሶ መጣ፡፡ በአህያ ላይ ተጭኖም ይጐበኘን ዘንድ መጣ፡፡ ነቢዩ ዘካርያስ የመንፈስ ቅዱስን እንዚራ ይዞ በደስታ ትንቢትን ለመናገር ይቻኰላል፡፡ እየደረደረም የጽዮንን ልጅ ይጠራታል፡፡” በማለት አስተምሯል፡፡
ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት የኾነችው በደመ ወልደ እግዚአብሔር የተመሠረተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ይኽነን በዓል በታላቅ ድምቀት፣ በማሕሌት፣ በቅዳሴ በተለይም ጌታ ቤተ መቅደሱን እየተመሰገነ መዞሩን በማሰብ በአራቱ መኣዝነ ቤተ ክርስቲያን ምስባክ እየተሰበከ ወንጌል እየተነበበ ከጾመ ድጓ ምራት እየተመራ በታላቅ ድምቀት በዓሉ ሲከበር፤ ሕዝበ ክርስቲያኑም በተመስጦ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዞ በግንባሩ አስሮ “ሆሣዕና ለወልደ ዳዊት” በማለት ፈጣሪያቸውን የባሕርይ አምላክ የኾነውን ንጉሠ ነገሥት፣ አምላከ አማልክት፣ የጌቶች ጌታ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተካከለውን ፈራጅ የኾነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያመሰግናሉ፡፡
ከበዓለ ሆሣዕና ረድኤት በረከት ያሳትፈን፡፡
መጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ